ባለፉት ስድስት ወራት ከ 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ የታክስ ቅሬታ መዝገብ ላይ ውሳኔ ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ስድስት ወራት ከ 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ የታክስ ቅሬታ መዝገብ ላይ ውሳኔ ተሰጥቷል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 25/2015 የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ባለፉት ስድስት ወራት በ316 የታክስ ቅሬታ መዝገቦች ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ውሳኔ መስጠቱን አስታወቀ።
የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን የ2015 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ አካሂዷል።

የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ሙሉጌታ አያሌው፤ ኮሚሽኑ ባለፉት ስድስት ወራት ለ320 መዝገቦች ውሳኔ ለመስጠት አቅዶ ለ316ቱ ውሳኔ መስጠት መቻሉን አስታውቀዋል።
በ2014 በጀት ዓመት በተለያዩ ምክንያቶች ውሳኔ ሳያገኙ የዞሩ 354 መዛግብትና ባለፉት ስድስት ወራት አዲስ የተከፈቱ 300 ቅሬታዎችን ጨምሮ 654 መዛግብት ለክርክር መቅረባቸውን ጠቅሰዋል።
ኮሚሽኑ ከቀረቡለት መዛግብትም በስድስት ወራት በ320 መዝገቦች ላይ አከራክሮ ውሳኔ ለመስጠት ከቀጠራቸው የታክስ ቅሬታ መዝገቦች መካከል ለ316ቱ ውሳኔ መስጠቱን ተናግረዋል።
ውሳኔ በተሰጣቸው መዛግብት ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ውሳኔ መሰጠቱንና በዚህም ኮሚሽኑ የዕቅዱን 98 ነጥብ 7 ከመቶ አፈጻጸም ማስመዝገብ መቻሉን አስረድተዋል።
ውሳኔ በተሰጠባቸው የቅሬታ መዛግብት የገቢዎች ሚኒስቴር በ107 መዛግብት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የጉሙሩክ ኮሚሽን በ209 መዛግብት ከ891 ሚሊዮን ብር በላይ ውሳኔ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።
ኮሚሽኑ በቀጣይ ስድስት ወራት የቅሬታ መዛግብት በተያዘላቸው ቀጠሮ ውሳኔ እንዲያገኙና ሥነ-ምግባር ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የኮሚሽኑ የፕላንና ለውጥ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር እዮብ አለማየሁ በበኩላቸው፤ የቅሬታ አገልግሎት ካገኙት ተገልጋዮች አብዛኞቹ በተሰጣቸው አገልግሎት መርካታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም የተገልጋይ እርካታን 96 ነጥብ 8 ከመቶ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።
ኮሚሽኑ የአገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ ተደራሽ ለማድረግ ሲስተም የማልማት ሥራውን በማጠናቀቅ በግማሽ ዓመቱ 250 ተገልጋዮች በቀጥታ በኦንላይን ምዝገባ ማካሄዳቸውን አመልክተዋል።
ቀደም ሲል ከ2011 እስከ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ከተሰነዱ መዛግብት ውስጥ 1ሺህ 885ቱን ዲጂታላይዝድ ማድረግ መቻሉን አቶ እዮብ ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን በጉምሩክ ኮሚሽንና በገቢዎች ሚኒስቴር ከፍተኛ የታክስ ክፍያ ተጥሎብናል የሚሉ የንግዱ ማኅበረሰብ አካላትን ቅሬታ የሚመለከትና ውሳኔ የሚሰጥ ተቋም ነው።