በሀረሪ ክልል የስንዴ ምርትን ለማስፋፋት በትኩረት ይሰራል---ርዕሰ-መስተዳደር ኦርዲን በድሪ

ሀረር (ኢዜአ) ጥር 25/2015 በሀረሪ ክልል የስንዴ ምርትን ለማስፋፋት በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ- መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

ርዕሰ-መስተዳድሩ በዘንድሮ የበጋ ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ በኤረርና ሶፊ ወረዳዎች በ150 ሄክታር መሬት ላይ በክላስተር እየለማ የሚገኘውን የስንዴ ማሳ ጎብኝተዋል፡፡

እንደ ሀገር ስንዴን በስፋት በማምረት ወደ ውጭ ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው አርሶ-አደሩ ስንዴን ለማምረት ከፍተኛ ተነሳሽነት እያሳየ መሆኑንም አብራርተዋል።

ቀደም ሲል በክልሉ ስንዴን ማምረት ያልተለመደ እንደ ነበር አስታውሰው ለአርሶ አደሩ በተፈጠረው ግንዛቤና ለአርሶ አደሩ በተደረገ ድጋፍ በክላስተር በለማው ስንዴ ላይ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም አትክልት የማምረቻ ወቅት እስኪደርስ ስራ ፈቶ ይቀመጥ እንደነበር ያስታወሱት ርዕሰ-መስተዳድሩ አሁን ላይ የአትክልት ማምረቻ ጊዜ እስኪደርስ ስንዴ በማምረት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ እየተመረተ ያለው የስንዴ ምርት የኑሮ ውድነቱን ከማረጋጋት ባሻገር የአርሶ አደሩ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

ርዕሰ-መስተዳደሩ በ150 ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረውን የስንዴ ማሳ ለማስፋፋት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም