የአገር ገጽታ ግንባታ፣ የንግድ፣ ልማትና ኢንቨስትመንት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል-የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ

237

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 24/2015 በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እየተከናወኑ ያሉ የአገር ገጽታ ግንባታ፣ የንግድ፣ ልማትና ኢንቨስትመንት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩን የበጀት ዓመቱን ስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል።

በሚኒስቴሩ የዕቅድ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ዓለማየሁ ሰውአገኝ፤ የተቋሙን የስድስት ወራት አፈጻጸም ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡ ሲሆን ተቋሙ ተልዕኮውን ለመወጣት የአሰራር ማሻሻያ አድርጎ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተከስቶ የነበረውን ግጭት መነሻ በማድረግ አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት ያልተገባ ጫና ፈጥረው እንደነበር አስታውሰው፤ ጫናውን በመቀልበስና እውነታውን ለዓለም በማሳወቅ ረገድ ሚኒስቴሩ የተሳካ የዲፕሎማሲ ሥራ አከናውኗል ብለዋል።

በተጨማሪም በሰላም ስምምነቱ ሂደትና በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ የታየው ቁርጠኝነት ''ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ'' ለሚለው እሳቤ መሰረት የጣለ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዳያስፖራው ጋር በመቀናጀት በአገር ገጽታ ግንባታ፣ በልማት፣ ኢንቨስትመንትና በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች የተከናወኑ ተግባራትም ጉልህ ፋይዳ እንደነበራቸው ጠቅሰዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላትም ሚኒስቴሩ እያከናወነ ባለው የለውጥ አሰራር አስፈላጊነትና አሁን ያለበትን ሁኔታ በሚመለከት ጥያቄና አስተያየት ሰንዝረዋል።

ከጎረቤት አገራት ጋር ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅም ላይ የተመሰረተ እንዲሆን እየተከናወነ ያለው ተግባር ምን እንደሚመስል አባላቱ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲና የዳያስፖራውን ተሳትፎ ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማጠናከር እየተከናወነ ስላለው ተግባርም እንዲሁ አንስተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም ባለፉት ሁለት አመታት በአገሪቱ ተከስቶ የነበረውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመሻገር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎችን ሲተገብር እንደነበር ገልጸዋል።

ከተለያዩ አገራት ጋር ኢትዮጵያ ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሟን ባስጠበቀ መልኩ እንዲከናወን ለማድረግ የተሰራው ሥራ ስኬታማ እንደነበርም አስረድተዋል።

በዚህ ረገድ የአገሪቱን ጥቅም በሚመለከት ያለው ዝግጁነትና ምላሽ የመስጠት ተግባር በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ መከናወኑ አሁን ለደረሰችበት መልካም ሁኔታ የጎላ ሚና ነበረው ብለዋል።

ከጎረቤት አገራት ጋር በድንበር አካባቢ የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ወዳጅነትንና ወንድማማችነትን ባከበረ መልኩ መፍትሄ ለማበጀት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፣ በወደብ አጠቃቀምና መሰል የዲፕሎማሲ ተግባራት ላይ ስኬታማ ሥራዎች ተከናውኗልም ነው ያሉት።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ፤ ሚኒስቴሩ በአስቸጋሪ ጊዜያት የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም ለማሳወቅ ያደረገውን ጥረት አድንቀዋል።

የአገርን ጥቅም ባስከበረ መልኩ ችግሮች እንዲፈቱ የሚያደርገው ጥረትም መልካም ጅማሮ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአገር ገጽታ ግንባታ፣ የንግድ፣ ልማትና ኢንቨስትመንት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባልም ብለዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም