ለኢትዮጵያ ክብርና ድል አድራጊነት የአትሌቶች የጋራ ስራና የአብሮነት መንፈስ እየተጠናከረ መሆኑን አሰልጣኞች ተናገሩ

180

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 24/2015 ለኢትዮጵያ ክብርና ድል አድራጊነት የአትሌቶች የጋራ ስራና የአብሮነት መንፈስ እየተጠናከረ መሆኑን የዘርፉ አሰልጣኞች ገለጹ።

ኢትዮጵያ የበርካታ ጀግና አትሌቶች መፍለቂያ ድንቅ አገር ለመሆኗ በኦሎምፒክ አደባባይ የተገኙ አንጸባራቂ ድሎች ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው።

የትውልዱ የድል ነጸብራቅ አብሳሪ በሆነው አትሌት አበበ ቢቂላ፤ የጀመረው የኢትዮጵያ አትሌቶች ድል በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬም ቀጥሏል።

በኢትዮጵያ አትሌቶች ተደጋጋሚ ድልና አስደናቂ አጨራረስ በመላው ዓለም የስፖርት አፍቃሪው አድናቆቱን ችሯል።

በአትሌቶቹ ድል ኢትዮጵያውያንም በደስታ ቁጭ ብድግ በማለት አጨብጭበው የደስታ እንባ የተራጩበት አጋጣሚ የበዛ ነው።

ከአትሌቶች ድል ጀርባ ያለው ጠንካራ ስራ እንዳለ ሆኖ የሀገር ፍቅርና መተባበር ለውጤቱ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑ አያጠያይቅም።

በስፖርቱ የድል ችቦ ለኳሾች የተጀመረው የአንድነትና የህብረት ስራ በእነ ሃይሌ ገብረስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ስለሺ ስህን፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ጌጤ ዋሜ፣ ብርሃኔ አደሬ እያለ ቀጥሎ የበለጠ ጎምርቶ ጣፋጭ ፍሬውን አቅምሶን አልፏል።

የአትሌቲክስ አሰልጣኝ ኮማንደር ቶሌራ ዲንቃ የአትሌቶች የቆየ አንድነትና ህብረት በተለያዩ ምክንያቶች ክፍተት እየታየበት እንደነበር ያምናሉ።

ለብሄራዊ ቡድን የተመረጡ አትሌቶች ሳይቀሩ በግል አሰልጣኞችና በማናጀሮቻቸው አማካኝነት በተበታተነ መልኩ ልምምድ በማድረግ የቡድን ስራንና የአብሮነት መንፈስ እየደበዘዘ እንደነበር ይናገራሉ።

በዚህም እንደ ሀገር በአለም አቀፍ ውድድሮች በተመዘገቡ ውጤቶች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳረፉን አስታውሰው አሁን ላይ ግን ለኢትዮጵያ ክብርና ድል አድራጊነት የአትሌቶች የጋራ ስራና የአብሮነት መንፈስ እየተጠናከረ መሆኑን ያምናሉ።

የአንድነትና የትብብር ስሜት መጠናከር በአትሌቲክስ ውጤት ላይ በጎ አስተዋጽኦ እንዳለው የሚያስረዱት ኮማንደር ቶሌራ ለቀጣይ ውጤቶች መልካም ጅምሮች እየታዩ ነው ብለዋል።

ሌላኛው አሰልጣኝ ኢንስፔክተር ደሳለኝ ፀጋ፤ የቡድን አንድነትና የእርስ በርስ ግንኙነት ከውጤት በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

ለብሄራዊ ቡድን የተመረጠ ማንኛውም አትሌት ከቡድን አጋሩ ጋር በመከባበርና በአንድነት መስራቱ ከውጤት በላይ አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ።

በመሆኑም አሁን ላይ ለብሄራዊ ቡድን የሚመረጡ አትሌቶች አንድ ላይ ልምምድ እንዲሰሩ መደረጉ የአትሌቲክስ ውጤት እንዲያንሰራራ እያደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ተወካይ ዮሐንስ እንግዳ፤ አንድነት ለምንም ጉዳይ ሃይልና ብርታት መሆኑን ጠቅሰው በተለይም ለአትሌቲክስ ውጤት የላቀ ሚና አለው ብለዋል።

ለዚህም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በስራ አስፈጻሚ አባላት ጭምር በአትሌቶች አንድነት ዙሪያ አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይህም በዓለም አቀፍ የውድድር መስኮች የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ያስቻለ ሲሆን ባለፈው ዓመት በኦሪገን በተደረገው የዓለም ሻምፒዮና የተገኘው ውጤት አንዱ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ የምንጊዜም ከፍተኛ የተባለውን ውጤት ማስመዝገቧን በማስታወስ ለተገኘው ድል የቡድን ስራና አንድነት የራሱን አስተዋጽኦ አሳርፏል ብለዋል።

በቀጣዩ ወር በአውስትራሊያ በሚካሄደው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ሁሉም አትሌቶች በአንድነት ልምምድ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው ጥሩ ውጤት እንደሚመዘገብም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የአትሌቶችን አንድነት በተመለከተ ፌዴሬሽኑ ወጥ አቋም ይዞ መስራቱ በትብብርና አንድነት የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም