ኢጋድ በቀጣናው የተከሰተውን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ በመመከት የጎላ አበርክቶ አድርጓል-የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ

161

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 24/2015 የምስራቅ አፍሪካ ልማት በየነ መንግሥታት /ኢጋድ/ በቀጣናው የተከሰተውን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ በመመከት የጎላ አበርክቶ ማድረጉን የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ገለጹ።

ኢጋድ በዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች በንቃት በመሳተፍ የአባል ሀገራቱን ወንድማማችነት ያማከለ ትብብርን እንደሚያሳድግም አመላክተዋል። 

ኢጋድ በቀጣናው ሀገራት ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ ሶስተኛውን ዓመታዊ ሪፖርት በኬንያ ሞምባሳ እየገመገመ ይገኛል። 

የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፤ ኢጋድ በቀጣናው የነበረውን ድርቅ፣ የበረሀነት መስፋፋትና ድህነትን በጋራ በመዋጋት ወንድማማችነትን ማጽናት አላማ አድርጎ ነው። 

በዚህም ኢጋድ አሁን ላይ ከዚህ ቀደም ከነበረበት አቅምና አበርክቶ የተሻለና ተጽዕኖ ፈጣሪ እየሆነ ነው ብለዋል። 

ባለፉት አምስት ዓመታት በቀጣናው ሀገራት የተከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ኢጋድን ክፉኛ እንደፈተኑት አስታውሰው ድርጅቱ የተከሰተውን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ በመመከት የጎላ አበርክቶ ማድረጉን ገልጸዋል። 

በተለይም፣ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ግጭትና ሽብርተኝነት በቀጣናው ላይ አደጋ እንዲያንዣብብ አድርገው እንደነበርም ተናግረዋል። 

በቀጠናው ሀገራት መካከል በፅኑ መሰረት ላይ የተገነባ ወንድማማችነትና ትብብር ለመፍጠር የተቋቋመው ኢጋድ ባለፉት ሶስት ዓመታት በሰላምና መረጋጋት ዙሪያ የጎላ ሚና ነበረው ብለዋል። 

በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለው የድንበር ውዝግብ በሰላም እንዲፈታ፣ የደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ግጭትን ለማስቆም የተሰሩ ስራዎችን በአብነት አንስተዋል፡፡ 

የሰሜን ኢትዮጵያን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የደቡብ አፍሪካና ኬንያው የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ኢጋድ ብርቱ ጥረት አድርጓል ብለዋል። 

የሰሜን ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት "የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን መፍታት እንደሚቻል ፈር የቀደደ ነው" ያሉት ዶክተር ወርቅነህ የኬንያ ፕሬዝዳንት ለነበራቸው ቁርጠኝነትም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል። 

ባለፉት ሁለት ዓመታት አምስት የኢጋድ አባል ሀገራት ኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያና ኬንያ ሀገራዊ ምርጫዎችን በሰላማዊ መንገድ በማጠናቀቅ የዴሞክራሲ ልምምድ እንዲፈጠር ማድረጋቸውንም በበጎ ጎኑ ጠቅሰዋል። 

እኤአ ከ2021 እስከ 2022 ድርቅ፣ ግጭትና የዩክሬን ጦርነት የኢጋድ አባል ሀገራቱን ፈትኗቸዋል ያሉት ዶክተር ወርቅነህ፣ በዚህም ከ36 ሚሊየን በላይ ህዝብ በድርቅ ተጎድቷል ብለዋል። 

በዚህም ኢጋድ ከዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት ጋር በመተባበር የሰብዓዊ አቅርቦት እንዲዳረስ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ 

በቀጣይም የአደጋ ቅነሳና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስልቶችን በማጠናከር ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ገንቢ ሚና ይጫወታል ብለዋል። 

ኢጋድ ከአፍሪካ ህብረት የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ጋር በመተባበር ይሰራል ለዚህም እኤአ እስከ 2025 የሚቆይ ስትራቴጂክ ዕቅድ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል። 

ኢጋድ በአባል ሀገራት መካከል ወንድማማችነትና ትብብር ለመፍጠር የቀጠናው ወጣቶች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ የኢጋድ የስራ አመራር አካዳሚ ያደርጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም