ቀጥታ፡

ኢጋድ ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ለሰላም ባበረከተችው አስተዋጽኦ ዕውቅና ሰጠ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 24/2015 ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በኢትዮጵያ የሰላም ድምጽ በመሆን ላበረከተችው አስተዋጽኦ የኢጋድ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰብ በሚል ዕውቅና ተሰጣት።

ኢጋድ ሶስተኛውን የድርጅቱ ዓመታዊ ሪፖርት በኬንያ ሞምባሳ እየገመገመ ይገኛል። 

የኢጋድ ዋና ጸሀፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፤ ቀጣናው በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በተፈተነባቸው ያለፉት ዓመታት የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የማይተካ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል። 

በዚህም በቀጠናውና በዓለም አቀፍ መድረኮች ጭምር በአየር ንብረት ለውጥ፣ አደጋ መከላከል፣ ሰላምና መረጋጋት፣ ሰብዓዊ ዕርዳታና በሌሎች ጉዳዮች የጎላ አበርክቶ የነበራቸው 21 ግለሰቦች ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል ። 

ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ሰላም እንዲሰፍን በተደጋጋሚ በተለያዩ መድረኮች የሰላም ድምጽ በመሆን ባበረከተችው በጎ ተግባር ኢጋድ እውቅና መስጠቱን ተናግረዋል። 

በየትኛውም መድረክ ለሰላም ዘብ በመቆም የመልካምነት አምባሳደር መሆኗን በተግባር አሳይታለች ሲሉም ዋና ጸሃፊው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም