የፋይናንስ ተቋማት አጠቃላይ ሀብት 2 ነጥብ 91 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ

196

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 24/2015 የፋይናንስ ተቋማት አጠቃላይ ሀብት 2 ነጥብ 91 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ ማሞ ምህረቱ ከፍይናንስ ዘርፍ ሀላፊዎች ጋር ውይይት እያደረጉ ነው።

አዲሱ ዋና ገዥ የፋይናንስ ዘርፋ ከቁጥጥር ባለፈ ከልማት አኳያ አካታች ስትራቴጂ ለመከተል አዲስ እይታን የሚፈልግ ነው ብለዋል።

የባንኩ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ የፋይናንስ ዘርፉ ያለበትን አጠቃላይ ሁኔታ ገለጻ ሲያደርጉ የፋይናንስ ተቋማት አጠቃላይ ሀብት፣ ብዛት፣ ተቀማጭ ሒሳብ እና ቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ዘርዝረዋል።

በማብራሪያቸው የፍይናንስ ተቋማት አጠቃላይ ሀብት 2 ነጥብ 91 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ገልጸዋል።ከዚህ ውስጥ የባንኮች ድርሻ 2 ነጥብ 8 ትሪሊዮን ብር እንደሆነ ጨምረዋል።

በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የባንኮች ቁጥር 31 የደረሰ ሲሆን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ደግም 18 መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ወደ 71 የሚጠጉ ፈቃድ ያልወሰዱ የፍይናንስ ተቋማት የሚገኙ ሲሆን 8 አዳዲስ ባንኮች እንደሆኑ ጠቁመዋል።

የፋይናንስ ተቋማት ቅርንጫፍ ቁጥር ከ12 ሺህ በላይ የደረሰ ሲሆን ከ10 ሺህ 200 በላይ የባንኮች ቅርንጫፎች ናቸው።

ምክትል ገዥው የፋይናንስ ዘርፉ ያለበት ሁኔታ ጤነኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

እየተካሄደ ያለው ውይይት ባንኩ በቀጣይ በትብብር መስራት የሚችልባቸውን ጉዳዮች ለማመላከት የሚረዳ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም