ግብርና በአገር ኢኮኖሚ ሞተር ሆኖ የወሳኝነት ሚና እየተጫወተ እንዲቀጥል ይሰራል -ሚኒስትር ግርማ አመንቴ

349

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 23/2015 ግብርና በአገር ኢኮኖሚ ሞተር ሆኖ የወሳኝነት ሚና እየተጫወተ እንዲቀጥል በይበልጥ እንደሚሰራ የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ተናገሩ።

ዶክተር ግርማ ከቀድሞው የግብርና ሚኒስትር አምባሳደር ዑመር ሁሴን ጋር የስራ ርክክብ አድርገዋል።

አዲሱ የግብርና ሚኒስትር ከሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች ጋርም ትውውቅ አድርገዋል።

ግብርና በአገር ኢኮኖሚ ሞተር ሆኖ የወሳኝነት ሚና እንዲጫወትና ሌሎች ዘርፎችን መምራቱን እንዲቀጥል ይሰራል ሲሉ ዶክተር ግርማ ገልጸዋል።

ግብርና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የተመዘገበው ውጤት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከሚኒስቴሩ ሰራተኞች፣ ተጠሪ ተቋማትና አርሶ አደሩ ጋር በቅንጅት የሚሰሩት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በዚህም ከፌዴራል እስከ ታችኛው የመንግሥት መዋቅር በተጠናከረ ሁኔታ በቅንጅት በመስራት ዘርፉን የበለጠ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራበት አመልክተዋል።

በግብርናው ዘርፍ ለተመዘገበው ለውጥ አምባሳደር ዑመር ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ገልጸው ለሰሩቱም ስራ ምስጋና አቅርበዋል።

የግብርና ዘርፉ ከራሱ ዕድገት አልፎ ሌሎች ዘርፎችንም እድገት ምክንያት መሆኑን ጠቁመው ለዚህም ደግሞ የተቋሙ አመራሮች ሠራተኞች በጋራ ያመጡት ውጤት ነው ብለዋል።

የቀድሞ የግብርና ሚኒስትር አምባሳደር ዑመር ሁሴን በበኩላቸው በግብርናው ዘርፍ ለውጥ እንዲመጣና ግብርናውን ለማዘመን በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

አዲሱ ሚኒስትርም የተጀመሩትን ሥራዎች የበለጠ በማጠናከር ግብርና የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የበለጠ መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመው መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።

ለሚኒስቴሩ አመራሮች፣ ሰራተኞችና አብራዋቸው ለሰሩት አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም