በአነስተኛ ግድቦች የመስኖ ልማትን ማጠናከርና የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጭን የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 23/2015 በአነስተኛ ግድቦች የመስኖ ልማትን ማጠናከርና የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጭን የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አሳሰቡ፡፡

የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የገበታ ለሀገር አካል በሆነው ሐላላ ኬላ ግምገማ ተካሂዷል።

በግምገማው በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች የተመዘገቡት ውጤቶች ለኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው እድገት ትልቅ ተስፋ የሰነቁ መሆኑ ተመልክቷል።

በዚህም የመስኖ ልማትን ጨምሮ የኃይል ዘርፉ፣ የወጪ ንግድ እንዲሁም በማዕድንና ኢነርጂ ዘርፍ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች የሚያበረታቱ መሆኑ ተገልጿል።

የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም እንደሚያመላክተው ዓመታዊ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት በ7 ነጥብ 5 በመቶ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በግምገማው የሥራ መመሪያና ቀጣይ አቅጣጫ ያስቀመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ በሁሉም ዘርፍ የተጀመሩ አበረታች የልማት ክንውኖች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስድስት ወራት አፈጻጸም አመርቂ ውጤት የታየበት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀጣይ በተለይም በአነስተኛ ግድቦች የመስኖ ልማትን ማጠናከርና የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጭን ማስፋት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

የዜጎችን የመጠጥ ውሃ ፍላጎት በሚፈለገው መጠን መመለስና የተሻለ ሥራ ማከናወንም የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ መሆን እንዳለበት አመላክተዋል።

የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በስድስት ወራት 48 ሺህ የውሃ ፓምፖችን በማስገባት ለመስኖ ሥራ የላቀ ሚና እንደነበረው አስታውሰው፤ ይህም ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

በቀጣይ የመስኖ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ከመደገፍ ባለፈ በየአካባቢው አነስተኛ የመስኖ ግድቦችን መሥራት ላይ ማተኮር ይገባልም ነው ያሉት።

በሕገ-ወጥ መልኩ የሚወጡ ማዕድናትን መቆጣጠርና ከውጭ የሚገቡ የግንባታ ግብዓቶች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ መሥራትም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆን አለበት ብለዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባለፉት ስድስት ወራት ለኢኮኖሚው ማደግ ትልቅ ሚና መወጣቱን አስታውሰው፤ በቀጣይ የዋጋ ግሽበትን በመቆጣጠር የተረጋጋ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመፍጠር መሥራት አለበት ብለዋል።

የሕገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን መቆጣጠር፤ በንግድ ሰንሰለቱ የሚስተዋሉ ዘርፈ-ብዙ ማነቆዎችን መፍታት ይገባልም ነው ያሉት።

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ለ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወደ ፊትም ተጨማሪ ሥራዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም