በምዕራብ ወለጋ ዞን እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ስራ ተከናውኗል

322

ጊምቢ (ኢዜአ) ጥር 23/2015 በምዕራብ ወለጋ ዞን በዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ስራ እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ስራ መከናወኑ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የዘንድሮው የበጋ ወራት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ባለፈው ሳምንት መጀመሩ ይታወሳል። 

በምዕራብ ወለጋ ዞንም በዚህ ዓመት በ42 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ስራ ለማከናወን ታቅዶ እስካሁን በተሰራ ስራ ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ስራው መሰራቱ ተገልጿል። 

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃለፊ አቶ ፋይሳ ሓምቢሳ ለኢዜአ እንደገለጹት እስካሁን የተሰራው ስራ የእቅዱን 10 በመቶ የሚሸፈን እንደሆነ ነው። 

በተፈጥሮ ኃብት ልማት ጥበቃ ስራው ከዚህ በፊት የተሰሩ ስራዎች የተሻለ ጥቅም በማስገኘታቸው ሕዝቡ በንቃት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ነው የገለጹት። 

በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች 483 ተፋሰሶች የተለዩ ሲሆን በዚህም ከ42 ሺህ ኪሎ ሜትሮ በላይ የተፋሰስ ልማት ስራዎች እየተከናወነ ነው፡፡ 

በዞኑ የበጋ ወራት የተፋሰስ ስራዎች አስቀድሞ እንደተጀመረ የተናገሩት ሃለፊው በዚህም አስካሁን 4ሺህ 332 ኪሎ ሜትር የተፋሰስ ስራን ጨምሮ የተለያየ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃዎች እንደተሰሩ ተናግረዋል። 

ባለፉት ዓመታት በዞኑ ተራቁተው ከልማት ውጪ የነበሩ አካባቢዎች ከ108 ሺህ 471 ሄክታር መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ስራ መከናወኑንም አስታውሰዋል። 

በተፋሰስ ስራው እየተሳተፉ የሚገኙ አርሶ አደሮች ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች የመሬት ለምነትን በመጠበቅ ድርቅና በረሃማነት እየቀነሰላቸው መሆኑን ገልጸዋል። 

ባለፉት አመታት በተፋሰስ ልማት የተገኘውን መልካም ተሞክሮ በማጠናከር የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ዘንድሮም የተፋሰስ ልማት ስራው ላይ በንቃት እየተሰተፉ እንደሚገኙም አርሶ አደሮች አስታውቀዋል። 

አርሶ አደር ዘውዴ ዳኖ ባለፉት ዓመታት በተሰሩት የተፋሰስ ስራዎች የደረቁ ወንዞች ውሃ መያዝ መጀመራቸውን ገልጸው አካባቢያቸው ወደ አረንጓዴነት እየተቀየረ መሆኑንም ተናግረዋል። 

ዘንድሮም እየተካሄደ ባለው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ቤተሰቦቻቸውን በማሳተፍ በስፋት ለመስራት መዘጋጀታቸዉን ነው የተናገሩት፡፡ 

አርሶ አደር ባልቻ ዳምሴ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በተሰሩ የበጋ ወራት የተፋሰስ ስራዎች ከምርት ውጪ የነበሩ የእርሻ መሬቶች፣ አካባቢያቸውም ወደ ለምነት እየተቀየረ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም