እየተመዘገበ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ዕድገት የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ከሚከናወኑ ተግባራት ጋር ማስተሳሰር ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

175

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 22/2015 እየተመዘገበ ያለውን የማክሮ (አጠቃላይ) ኢኮኖሚ ዕድገት የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ከሚከናወኑ ተግባራት ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

የ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የገበታ ለሀገር አካል በሆነው ሐላላ ኬላ ተካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ባለፉት ስድስት ወራት የዜጎችን ተጠቃሚነት እውን የሚያደርጉ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

በተለይም የግብርናው ዘርፍ በቀዳሚነት ለውጥ የመጣበት መሆኑን ጠቁመው በሰብል ምርት ከፍተኛ የሆነ ዕድገት የተመዘገበበት መሆኑንና በዚህም በርካታ ከውጭ የሚገቡ የሰብል ምርቶችን በአገር ውስጥ ማምረት መቻሉን ጠቅሰዋል።


የወጪ ንግድን ከማሳደግ አኳያ በተለይ የቡና ምርት በከፍተኛ መጠን ወደ ውጪ በመላክ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን አመልክተዋል።

በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ እምርታ የተመዘገበው አርሶ አደሩን ለልማት በማነሳሳት በክላስተር በመስራት እና ቴክኖሎጂ በመጠቀም መሆኑን ተናግረዋል፡፡


በተጨማሪም በፌደራልና በክልል መንግስታት ለመስኖ ስራ የሚያግዙ 48 ሺህ ፓምፖች ባለፉት ስድስት ወራት ለአርሶ አደሩ እንዲሰራጩ መደረጉ ለተመዘገበው ውጤት የላቀ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።

በግብርናው ዘርፍ ልማት የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ከሚከናወኑ ተግባራት ጋር በማስተሳሰር በምግብ ራስን መቻልና ለገበያ ማቅረብ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ነው የገለጹት።

አሁን ላይ ያለውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠርም መፍትሔው ላይ ያተኮረ ስራ ያስፈልጋል ብለዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ገቢን ከመሰብሰብ አንጻር ከፍተኛ ስራ መሰራቱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከጥቅል አገራዊ ዕድገት አንጻር ግን አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡


ለዚህም ኮትሮባንድን በመቆጣጠር፣ ቴክኖሎጂን በማስፋፋትና አሰራርን በማዘመን ጭምር ገቢን በሚፈለገው ልክ መሰብሰብ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።


"ኢትዮጵያ ታምርት" በሚለው የንቅናቄ መድረክ የተመዘገበው ውጤት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይም የአገር ውስጥ አምራቾችን የበለጠ መደገፍ ይገባል ብለዋል።

በስድስት ወራት የታየውን ውጤታማ አፈጻጸም በማስቀጠል የተገኙ የማክሮ ኢኮኖሚ ድሎችን በማስቀጠል የበለጠ ውጤታማ ለመሆን በትጋት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም