መንግስት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት እንዲያጠናክር ተጠየቀ

117

አርባ ምንጭ (ኢዜአ) ጥር 22/2015 መንግስት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል የጋሞ ዞን ነዋሪዎች ጠየቁ።


የፌዴራል፣የደቡብ ክልልና የጋሞ ዞን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በወቅታዊ፣ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከጋሞ ዞን ነዋሪዎች ጋር ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ ተወያይተዋል፡፡


በውይይት መድረኩ ከተሳተፉ መካከል የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሽታዬ ዘካሪያስ ለኢዜአ እንዳሉት የለውጡ መንግስት በፈተና ታጅቦ ለዘመናት ያልተፈቱ ችግሮችን በመቅረፍ በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ለውጥ አስመዝግቧል፡፡


ይሁንና በመሠረታዊ የሸቀጣ ሸቀጥ አቅርቦትና የኑሮ ውድነት፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በቅጥርና ዝውውር ፣ በአገልግሎት አሰጣጥና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ አሁንም ያልተፈቱ ችግሮች መኖራቸውን አመልክተዋል ።

የኢንዱስትሪ ፈር ቀዳጅ የነበረው የአርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ መዳከም፣ የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ ህልውና አደጋ ላይ መውደቅ፣ ከኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ በርካቶች በወሰዱት መሬት ላይ ተገቢውን ልማት ያለማከናወን ሌሎች ሊፈቱ የኘሚገባቸው ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል ።


መንግስት በተለይም የዘርፎቹ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በፍጥነት እንዲፈታ ጠይቀዋል ፡፡


"ህዝቡም በተለይ ልማት መጠየቅ ብቻ ሳይሆን መንግስት እያካሄደ ባለው የለውጥ ጉዞ ድርሻዬ ምንድ ነው በማለት ለሀገሪቱ ህዳሴ መረጋገጥ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል" ብለዋል፡፡


"ከዚህ በፊት በአካባቢው ለበርካታ ፕሮጀክቶች ግንባታ መሠረተ ድንጋይ ከመጣል ባለፈ ተገንብተው ለአገልግሎት የሚበቁ ፕሮጀክቶች ግን እንብዛም ሲስተዋሉ አልነበረም " ያለው ደግሞ የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ ወጣት አምሳሉ መንግስቱ ነው።


"የለውጡ መንግስት ግን የጀመራቸውን ፕሮጀክቶች በአግባቡ በመገንባት የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው" ብለዋል።


ከለውጡ በኋላ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቋል።


"መንግስት ያለ ህዝብ፣ህዝብ ደግሞ ያለ መንግስት መኖር አይቻልም" ያለው ወጣቱ በጋሞ አባቶች ምክር ተኮትኩተን እንዳደግን ሁሉ በመንግስት የታቀዱ የህዝብ ልማቶች እንዲሳኩ የበኩላችንን እንወጣለን " ሲል አክሏል።


በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ዘርፍ አስተባባሪ ሚኒስትር አቶ አብርሃም አለኸኝ በበኩላቸው መንግስት ከህዝቡ ፍላጎትና የመልማት ጥያቄ ውጭ መሆን እንደማይችል ተናግረዋል ።


በተለይ የመድረኩ ተሳታፊዎች የስራ አጥነት ችግርን አስመልክተው ላነሱት ጥያቄ መንግስት ችግሩን ለመፍታት የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡


"ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በመዋቅር ደረጃ ህዝባችንን አላረካንም" ያሉት ሚኒስትሩ "ከመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር በጋራ ልንፈታ ይገባል" ብለዋል፡፡


ሚኒስትሩ አክለውም "ሀገራዊ ለውጡን ለማሳካት ኢትዮጵያዊያን በመደመር ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን ጠብቀን የበኩላችን ልንወጣ ይገባል" ብለዋል።


የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በበኩላቸው የአርባ ምንጭ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ለአካባቢውና ለሀገር ኢኮኖሚ ፈር ቀዳጅ መሆኑን ጠቁመው ኢንዱስትሪውን የማጠናከር ስራ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን አመላክተዋል ።


ከመሰረታዊ የሸቀጣሸቀጥ አቅርቦት ጋር በተያያዘ በተለይም በሲሚንቶ አቅርቦት በኩል መጠነኛ የዋጋ ለውጥ እየታየ መሆኑን ጠቁመው ችግሩን ለማሶገድ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል ።


በውይይቱ ከጋሞ ዞን የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም