በመዲናው የብዙሃን ትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪ ወጥ በሆነ መንገድ ባለመተግበሩ ለእንግልት ዳርጎናል - አገልግሎት ተጠቃሚዎች

170

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ጥር 22/2015 በአዲስ አበባ በቅርቡ በብዙሃን ትራንስፖርት ላይ የተደረገው የታሪፍ ጭማሪ በአግባቡ ባለመተግበሩና በስምሪት አሰጣጥ ችግር ለእንግልት መዳረጋቸውን የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተናገሩ።

የጥር ወር ነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተከትሎ በአዲስ አበባ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ የአገልግሎት መስጫ ታሪፍን ማሻሻያ መደረጉ ይታወሳል።

በብዙሃን ትራንስፖርት ላይ የተደረገው የታሪፍ ማሻሻያ አተገባበር ወጥ አለመሆንና የስምሪት አሰጣጥ ችግር መኖሩን አስተያየት ሰጪዎች ለኢዜአ ገልጸዋል።

"ቀድሞ ለአጭር ርቀት ከሚከፈለው የአገልግሎት ክፍያ ከእጥፍ በላይ እየተጠየቅን ነው ይህ ደግሞ መንግስት ካወጣው ታሪፍ ጋር የሚቃረን ነው" ብለዋል።

መገናኛ አካባቢ ያገኘናቸው ተጠቃሚዎች እንደሚሉት ከዚህ በፊት "ከፒያሳ እስከ አስኮ ሶስት ብር ይከፈል የነበረው ታሪፍ ቀድሞ ከምንከፍለው 5 ብር ጨምሮ 8 ብር እየተጠየቅን ነው" ብለዋል።

ወደ ቄራ ለመሄድ አውቶቢስ እየጠበቁ ያገኘናቸው አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው የታሪፉ አተገባባር ሕጉንና የጉዞ ርቀቱን ታሳቢ ያላደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች መንግስት ያወጣውን የታሪፍ ጭማሪው በአግባቡ ባለመተግበራቸው "ሕዝቡን ለምሬት ዳርገውታል" ሲሉ አስተያየት ሰጪዎቹ አክለዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ አውቶቢሶች ሕብረተሰቡን በተገቢው መንገድ እያገለገሉ እንዳልሆነና ስምሪቱ ላይ ያሉ ችግሮች ሊፈቱ እንደሚገባ ነው አስተያየት ሰጪዎቹ ያስገነዘቡት፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት የአንበሳና ሸገር አውቶቢሶች ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ተወካይ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ፍስሃ በበኩላቸው "የተገልጋዩን ቅሬታዎች መሰረት በማድረግ የእርምት እርምጃ ይወሰዳል" ብለዋል።

ሁለቱ ድርጅቶች ተጣምረው ለሕብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ላይ መሆናቸውንና በተለይ የስምሪት ችግሮችን ለመፍታት ከስልጠና ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የሕዝቡን ቅሬታዎች ሕጉንና ኪሎ ሜትሩን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለማስተካከል እንደሚሰራም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም