የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከተቋማት ጋር ያለው የቅንጅት ማነስ በአገር ሃብት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው-ምክር ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከተቋማት ጋር ያለው የቅንጅት ማነስ በአገር ሃብት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው-ምክር ቤቱ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 22/2015 የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከተቋማት ጋር ያለው የቅንጅት ማነስ በአገር ሃብት ላይ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ በአፋጣኝ ሊያስተካክል እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ባቀረበው በቀድሞው የፌዴራል የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ የ2013/14 በጀት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ውይይት አድርጓል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሰረት ዳምጤ ባቀረቡት ሪፖርት አንዳንድ የመሰረተ ልማት ስራዎች በስታንዳርድ መሰረት ያልተሰሩና አገራዊ የመሰረተ ልማት የዕድገት አቅጣጫ የሚመራበት ማዕቀፍ የሌላቸው መሆኑ በግኝቱ ተረጋግጧል ።
ከአስፈጻሚ ተቋማት ጋር ያልተናበበና ያልተቀናጀ የመሰረተ ልማት ስራዎች እየተሰሩና የመሰረተ ልማት ቅንጅት ስራ ፍቃድ መመሪያ እንደሌለው አስረድተዋል።
በመሰረተ ልማት ግንባታ ወቅት አንዱ ተቋም በሌላ ላይ ጉዳት ሲያደርስ ለጉዳቱና ለባከነው ሀብት ግልጽ የካሳ አከፋፈልና የተጠያቂነት አሰራር ስርዓት እንደሌለም ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በቀረበው ሪፖርት ላይ በሰጡት አስተያየት በኦዲት ግኝቱ መሰረት ኤጀንሲው አገራዊ የተቀናጀ መሰረተ ልማት መሪ ፕላን በከተሞች የሚሰሩ ማስተር ፕላኖች ከመንገድ በስተቀር ሌሎች አላዘጋጀም።
በዚህም ምክንያት በመሰረተ ልማት ላይ የሚሰሩ ተቋማት አንዱ ሲገነባ ቀድሞ በተገነቡ ሌሎች መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት በማድረስ በአገር ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው ሲሉም አክለዋል።
የምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ አራሬ ሞሲሳ እንዳሉት ይህን ተቋሙ አዳዲስ የሚገነቡ ከተሞች በዘፈቀደ ያለፕላን እየተገነቡ ይገኛሉ።
ይህም በቀጣይ በማስተር ፕላን ለማስተካከል አስቻጋሪ ሁኔታ እየፈጠረ ይገኛል ያሉት ወይዘሮ አራሬ ሚኒስቴሩ ይህን ለማስተካከል ምንም እያደረገ አይደለም ብለዋል።
በመሆኑም ተቋሙ እነዚህ ጉዳዮች በህብረተሰቡ ዘንድም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየፈጠሩ መሆኑን ተረድቶ ለማስተካከል በቀጣይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የመሰረተ ልማት መስመሮች የተቀበሩበትን ቦታ በትክክል የሚያመላክት ማስረጃ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ አስተዳደር ስርዓት አለመዘርጋቱ ችግሩን ውስብስብ ማድረጉንም አንስተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው ተቋሙ በቅንጅት ባለመሰራቱ የለሙ መሰረተ ልማት የሚፈርሱበት እና አንዱ ተቋም ሲገነባ ሌላው የሚያፈርሰበት ሁኔታ ሊኖር አይገባም ሲሉም አሳስበዋል።

በአገሪቱ የሚሰሩ መሰረተ ልማቶችን የማቀናጀት እና ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ላይ ያለውንም ክፍተት ሊያስተካክል ይገባል ብለዋል።
ሚኒስቴሩ የኦዲት ማሻሻያውን እስከ ጥር 30 ቀን 2015 ዓም ድረስ እንዲያቀርብ እና ግኝቱንም የዕቅዱ አካል እንዲያደርግ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።
የመሰረተ ልማት የመረጃ አስተዳደር ስርዓት በተቻለ ፍጥነት ሊዘረጋ ይገባል፣ እያንዳንዱ የመሰረተ ልማት ዝርጋታና ግንባታ በመያዝ የአገር ሀብት ከብክነት ሊያድን እንደሚገባ አሳስበዋል።
የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ከተቀናጀ የመሰረተ ልማት ግንባታና ዝርጋታ አንጻር ለብልሹ አሰራር የሚዳረጉ ክፍተቶችን በማጥናት ውጤቱን በሶስት ወራት ውስጥ ሊያሳውቅ ይገባል ብለዋል።
ተቋሙ ወጥ የሆነ የካሳ አከፋፈል ስርዓትም ሊዘረጋ እንደሚገባም እንዲሁ።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የመሰረተ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ በበኩላቸው የቀረቡትን ጉዳች መቀበላቸውን ገልጸው በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በተለይ የካሳ ክፍያ በታችኛው የመንግስት ማዋቅር የሚወሰን በመሆኑ ወጥነቱ ላይ ችግር መኖሩን ገልጸው በቀጣይ ለማሻሻል የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ ሲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
መረጃዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መዝግቦ ለመያዝ የጂኦ እስፓሻል ጥናት በማድረግ በቀጣይ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የፌዴራል የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ የፌደራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣ አዋጅ 2014 መሰረት ከከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ጋር መዋሃዱ ይታወሳል።