ዳያስፖራው ኢንዱስትሪ ጨምሮ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መዋዕለ ንዋዩን እያፈሰሰ ነው - የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማህበር - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው ኢንዱስትሪ ጨምሮ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መዋዕለ ንዋዩን እያፈሰሰ ነው - የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማህበር

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ጥር 22/2015 ዳያስፖራው ኢንዱስትሪ ጨምሮ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተው መዋዕለ ንዋዩን እያፈሰሰ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማህበር አስታወቀ።
በንግድና ኢንቨስትመንት ለመሰማራት በሚያደርጉት ጥረት የሚጋጥሟቸውን ችግሮች ለመቀነስ እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።
የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማህበር የቦርድ ፕሬዝዳንት አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ፤ ማህበሩ ሰፊ ልምድና እውቀት ያላቸው አካላትን በአመራርነትና በአባልነት ያቀፈ ነው።
የማህበሩ አባላት በውጭ ያካበቱትን እውቀትና ልምድ ወደ አገራቸው በማምጣት በመገናኛ ብዙሃን፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በቴክኖሎጂና በአቪዬሽን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛል ብሏል።
በቀጣይም የማህበሩን አባላት በማሳደግ በተለያዩ ዓለማት የሚኖሩ ዜጎች በአገራቸው የሚገኙ የኢንቨስትንመት ጸጋዎችን እንዲያለሙ እንደሚሰራ አመልክተዋል።
በንግድና ኢንቨስትመንት ለመሰማራት በሚያደርጉት ጥረት የሚጋጥሟቸውን ችግሮች ለመቀነስም ማኅበሩ እየሰራ መሆኑንም ነው አርቲስት ዘለቀ የገለጸው።
ማህበሩም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የአገራቸውን የሕግና የፖሊሲ የአሰራር ሥርዓት እንዲያውቁ በማድረግ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተው የሚሰሩበትን እድል እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግሯል።
በተመሳሳይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵዊያን የኢትዮጵያን ልማት በመደገፍ አገራቸውን ለመለወጥ ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው አመልክቷል።
በተፈጠረው አሰራር የተሻለ ምላሽ እየተገኘ መሆኑን ጠቁሞ፤ የማህበሩ አደረጃጀትም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከዚህ ቀደም የሚያጋጥሟቸውን "ውጣ ውረዶች እየቀነሰ" ቀንሷል ብሏል።
የአዲስ አበባ ዳያስፓራ ማህበር የቦርድ አባል ተስፋዬ ውቤ፤ በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ከኢንቨስትመንት ሕግና ፖሊሲ ጋር የሚያነሷቸውን ችግሮች ለማሻሻል ማህበሩ ከመንግሥት አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመንግሥት በኩል የተሻለ የአሰራር ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለያዩ ዓለማት የሚኖሩ ዜጎችም ከማኅበሩ ጋር በመሥራት ለአገር እድገት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ከሶስት ዓመታት በፊት የተመሰረተው የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማህበር 400 የሚጠጉ አባላት ያሉት ሲሆን፤ ኢትዮጵዊያን በአገራቸው የልማት እንቅስቃሴ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መደገፍን ዓላማው አድርጎ የተቋቋመ ሲቪክ ድርጅት ነው።
በውጭ የሚኖሩ ዜጎችም በማህበሩ ገጽ "aadiaspora.org" ገብተው አባል በመሆን የሚፈልጉትን መረጃ አግኝተው በኢንቨስትመንት ዘርፍ መሰማራት የሚችሉበት እድል መፈጠሩም ተገልጿል።