የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የዓሣ ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል የሚያስችል ምርምር እያካሄደ እንደሚገኝ አመለከተ

212

ሐዋሳ፣ ጥር 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በምርምር የዓሣ ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል ለሌማት ትሩፋት የልማት እንቅስቃሴ መሳካት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

በዩኒቨርሲቲው የዓሣ ምርምርና ትምህርት ማዕከል ኃላፊ ዶክተር ካሳዬ ባልከው ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ዩኒቨርሲቲው የሀዋሳ ሐይቅን ማዕከል አድርጎ ባካሄዳቸው ጥናቶች ጥንቃቄ በጎደለው የዓሣ ማስገር ሥርዓት የዓሣ ምርት ተመናምኗል።

ችግሩን ለመቀልበስና በሐዋሳና አካባቢው ላይ ዘላቂ የሆነና እያደገ የሚሄድ የዓሣ ምርት እንዲኖር የምርምርና ትምህርት ማዕከል ተቋቁሞ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የሥነ ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሌማት ትሩፋትና መሰል ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ገቢራዊ እየተደረጉ በመሆኑ ይህንን እንቅስቃሴ በምርምር ለመደገፍ ዩኒቨርስቲው እየሰራ ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድ ዓሣ በንጥረ ነገር ይዘቱ ከሌሎች የምግብ ዓይነቶች እጅግ የተሻለ ስለሆነ ዩኒቨርሲቲው በምርምር የተደገፈ የዓሣ ምርትና ምርታማነትን የማሻሻል ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

ማዕከሉ የተሻሻሉ የዓሣ ዝርያ ጫጩቶችን በብዛት የማምረትና ለተጠቃሚዎች የማዳረስ፣ የተመጣጠኑና በቀላሉ ሊዘጋጁ የሚችሉ መኖዎች ላይ ምርምር የማድረግና ግኝቶችን የማላመድ እንዲሁም ሌሎች የምርምርና ስርፀት ሥራዎችን እያቀላጠፈ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

አርሶ አደሩ በጓሮው ውስጥ ዓሣ አምርቶ እንዲመገብና ለገበያ አቅርቦ ገቢ እንዲያገኝ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ገልፀው፤ በኩሬ ዝግጅትና ዓሣ አመራረት ላይ ተከታታይ ሥልጠናዎችን በመስጠት ጫጩቶችን በስፋት እያቀረብን እንገኛለን ብለዋል።

እስከሁን 450 የሚጠጉ በሐዋሳና አካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች በጓሯቸው ኩሬ ማዘጋጀት የቻሉ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው ከ130 ሺህ በላይ የዓሳ ጫጩቶችን ማሰራጨቱን አስረድተዋል።

በኩሬዎች ዓሣ የማምረት ተግባር በሀዋሳ ሐይቅ ብቻ የሚደረገውን ዓሣ ማስገር በመቀነስ ማህበረሰቡን በዘላቂነት ተጠቃሚ የማድረግ ግብ እንዳለው ተናግረዋል።

በሐይቁ ውስጥ የጫጩት እጥረት ሲገጥምም አማራጭ የጫጩት ምንጭ በመሆን የዓሣ ምርት መመናመንን የማስቀረት ሚና እንዳለውም አብራርተዋል።

ዓሣ እንደ ሀገር ገና ያልተጠቀምንበት እምቅ ሀብታችን ነው ያሉት ዶክተር ካሳዬ፤ ዩኒቨርሲቲው ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት በዓሣ ምርት ሞዴል አርሶ አደሮችን እያፈራ እንደሆነ ተናግረዋል።

በኩሬ ውስጥ የሚከናወን የዓሣ ምርት ሥራ ከሌሎች ምርቶች ጋር ለማቀናጀት ምቹ እንደሆነ ጠቅሰው፤ አርሶ አደሩ ዓሣ፣ ዶሮ እና አትክልትን ተመጋጋቢ በሆነ መንገድ እንዲያመርት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

በይርጋዓለም ከተማ የሳምራ ዓሣና አትክልት አምራች ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ዘማች አድነው በከተማ አስተዳደሩና በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ ከአንድ ዓመት በፊት ኩሬ በማዘጋጀት ዓሣ እንዲሁም ዶሮ እና አትክልት ማምረት መጀመራቸውን ተናግሯል።

ዩኒቨርሲቲው ያቀረበላቸው አንድ ሺህ የዓሣ ጫጩቶች በሶስት ወር ውስጥ እደደረሱ ገልጿል።

በአሁኑ ወቅት ማህበሩ የራሱን የዓሣ ምግብ ቤት በይርጋዓለም ከተማ በመክፈት በፊሌቶ፣ በጥብስና በሾርባ መልክ ለተጠቃሚዎች እያቀረበ ይገኛል ብሏል።

የከተማዋ ነዋሪዎች የዓሣ ፍላጎትና አቅርቦት የማይመጣጠን መሆኑን ጠቅሶ፤ በዘርፉ መስራት አዋጭ መሆኑን አመልክቷል።

በይርጋዓለም ከተማ አስተዳደር የከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ባለሙያ አቶ ልዑልሰገድ መኮንን በከተማዋ ዙሪያ ለዓሣ ምርት ምቹ የሆኑ ወንዞችና ምንጮች እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በከተማዋ ዙሪያ እስከ 40 ቶን ዓሣ በዓመት ማምረት የሚያስችል አቅም እንዳለ ገልፀው፤ በአሁኑ ወቅት እየተመረተ ያለው 20 ቶን ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

ከተማዋ ባላት አቅም ልክ ዓሣን ማምረት እንዲቻል ብሎም ማህበረሰቡ በስፋት ዓሣን የመመገብ ባህሉ እንዲዳብር ለማድረግ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲና ከሲዳማ ክልል እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ ጋር በመተጋገዝ እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም