የስራና ክህሎት ሚኒስቴር የስራ ፍላጎትን በማነሳሳትና በስልጠና በመደገፍ ሰዎችን አምራች ሀይል ማድረግ እንደሚቻል ገለጸ

ጅማ፣ ጥር 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) የስራ ፍላጎትን በማነሳሳትና በስልጠና በመደገፍ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የሚገኝን ሰው አምራች ሀይል ማድረግ እንደሚቻል የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ።

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በጅማ ከተማ ባዘጋጀዉ መድረክ አካታች የስራ እድሎችን በመፍጠር አካል ጉዳተኞች፣ ልዩ ፍላጎት የሚሹ ወገኖችንና ቤት የሌላቸዉን ወገኖች የስራ እድል ተጠቃሚ በሚሆኑበት ሁኔታ ላይ እና ሚኒስቴሩ በስድስት ወራት ውስጥ የሰራዉን የስራ እድል ፈጠራ ሪፖርት ላይ ዉይይት ተደርጓል።

በውይይት መድረኩ ላይ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንደገለጹት፤ ሰዎች አምራች ሃይል እንዲሆኑ የስራ ፍላጎታቸውን ማነሳሳትና በስልጠና መደገፍ ይገባል።

በተለያየ ምክንያት ተንቀሳቅሰው መስራት የማይችሉ ወገኖችን፣ ቤት የሌላቸዉን፣ ከስደት ተመላሾችን፣ ልዩ እገዛ የሚሹ ሰዎችን ያካተተ እና ግለሰቦቹ መስራት በሚችሉበት ሁኔታ የስራ እድል ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ሚኒስቴሩ አካታች የስራ እድል መፍጠር የሚያስችል ጥላ የተሰኘ ፕሮጀክት ቀርጾ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አቶ ንጉሱ ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በ19 ወራት 24 ሺህ ለሚሆኑ ወገኖች ስልጠና መስጠቱን አስታውሰው፤ ከነዚህም ዉስጥ 11 ሺህ 700 ለሚሆኑ ስራ ያልነበራቸዉ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በዚህ አመት ለ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸው፤ በግማሽ አመት አፈጻጸም ለ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች የስራ እድል እንደተፈጠረ አመላክተዋል።

የጅማ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ዋሲሁን ግርማ በበኩላቸዉ ፕሮጀክቱን ለመተግበር በሚደረገዉ ጥረት የከተማ አስተዳደሩ የበኩሉን እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ባጠቃላይ ባለፉት 6 ወራት ከ13 ሺህ በላይ ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

በተለይም የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በሚሰራዉ የአካታች የጥላ ፕሮጀክትን ለማገዝ የጅማ ከተማ 20 የመሸጫና የመስሪያ ሼዶችን ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም