የብልፅግና ፓርቲ የሃረሪ ክልል ወጣቶች ሊግ አባላት ፅንፈኝነትን እና ሌብነትን በመታገል ለዘላቂ ልማት እንደሚተጉ ገለጹ

ሀረር (ኢዜአ) ጥር 21 / 2015 የብልፅግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ወጣቶች ሊግ አባላት ፅንፈኝነትን እና ሌብነትን በመታገል የኢትዮጵያን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ እንደሚተጉ ገለጹ።

የብልፅግና ፓርቲ የሃረሪ ክልል ወጣቶች ሊግ "ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ ብልፅግና የሚተጋ ወጣት" በሚል ርእስ በ1ኛ መደበኛ ጉባኤው ባሳለፋቸው ውሳኔዎች ላይ ከአባላቱ ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

ኢትዮጵውያን ወጣቶች ከጥንት ጀምሮ ለአገር እድገት ያደረጉትን ተጋድሎ የሚያሳይ መነሻ ፅሁፍ ላይ በመወያየት ወጣቱ አሁንም በግብርናው ዘርፍ በትጋት በመስራት እመርታዊ ለውጥ በማስመዝገብ ኢኮኖሚውን በማጎልበት አገሪቱን ከኢኮኖሚ ጫና ማውጣት እንዳለበት በጽሁፉ ተመላክቷል።

በውይይት መድረኩ አስተያየታቸውን የሰጡት የሊጉ አባላት ወጣት መሃመድ ዩሱፍ፣ ወጣት ጀማል አብዲ እና ወጣት መሃመድ አብዱላሂ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የለውጥ ስራ ከዳር ለማድረስ ጽንፈኝነትና ሙስናን መከላከል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በወጣት ሃይል ማሳካት የማይቻል ነገር እንደሌለ ጠቅሰው አንድነትን አስጠብቆ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡

አገሪቱ የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ ለማረጋገጥም ከመከፋፈል ይልቅ አንድ በመሆን ብሎም ለስራ ያላቸውን አመለካከት በማስተካከል የበኩላቸውን ሃላፊነት እንደሚወጡ ገልፀዋል፡፡

የጥንት አባቶች የሰሩትን ታሪክ መተረክ ብቻ ሳይሆን ትውልዱ ወደፊት የሚታወስበትን አሻራ ለማሳረፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በአገሪቱ ለመጣው ለውጥ የወጣቱ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰው፤ ለውጡ በጽንፈኝነትና በሌብነት እንዳይደናቀፍ መስራት እንዳለባቸው መገንዘባቸውን ጠቅሰዋል።

ለዚህም አስፈላጊውን ትግል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ ወጣት ሙራድ አሚን በበኩሉ መንግስት ሌብነትን በመዋጋት ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራውን ስራ ማገዝ እንደሚገባ አመልክቷል።

የብልፅግና ፓርቲ የሃረሪ ክልል ወጣቶች ሊግ ሰብሳቢ ወጣት ሸሪፍ ሙሜ በወጣት ሊጎች የተጀመሩ የበጎ ፈቃድ ተግባራት እና የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጿል።

ወጣቱ የጀመረውን የለውጥ ትግል አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል አረጋግጦ፤ ወጣቱ ትውልድ በእቅድ በመመራት የተሻለ ነገን ለመፍጠር ሊተጋ እንደሚገባ አስገንዝቧል።

በውይይት መድረኩ ላይ የደቡብ እና የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳር ወጣቶች ሊግ አመራሮች እንዲሁም የሃረሪ ክልል የወጣቶች ሊግ አመራር እና አባላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም