አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ፕሮጀክት ቀርፆ ጥናት መጀመሩን ገለፀ

አርባ ምንጭ፣ ጥር 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ የትምህርት ጥራት ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የሚያስችል ፕሮጀክት ቀርጾ ጥናት መጀመሩን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲዉ በትምህርት ጥራት ተግዳሮቶችና መፍትሄዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት በአርባ ምንጭ ከተማ ተወያይቷል።

የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ተባባሪ ፕሮፌሰር በሃይሉ መርዴኪዮስ እንዳስታወቁት፤ ከትምህርት ጥራት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመቅረፍ “የተማሪዎች ውጤት አፈጻጸም ማሻሻያ” በሚል ስያሜ ፕሮጀክት ተቀርጾ ጥናት ተጀምሯል።

ዘንድሮ የተመዘገበው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ውጤት በትምህርት ጥራት ላይ በስፋት መስራት እንደሚገባ ማሳየቱንም ገልጸዋል።

መንግስት የተለያዩ የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ስርአቶች፣ ፖሊሲዎችና ደንቦችን በመቅረጽ በርካታ ስራዎችን ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በትምህርት ሂደት፣ በግብአት አቅርቦትና በትምህርት አመራሮች ክፍተት መቅረፍ ላይ የተጠበቀው ውጤት አለመመዝገቡ የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤትን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የተቀረፀው ፕሮጀክት ተማሪዎች ራዕይ እንዲኖራቸውና በትምህርታቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።

አስፈላጊ የትምህርት ግብአት እንዲሟላና የትምህርት ባለድርሻ አካላት በተሟላ መልክ የበኩላቸውን እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑን ተባባሪ ፕሮፌሰር በሃይሉ ጠቁመዋል።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ትምህርትና ስነ-ባህርይ ሳይንስ ትምህርት ቤት የምርምር ስራ አስተባባሪና የተማሪ አካዳሚክ ስኬት ማሳለጫ ፕሮጀክት ዋና ተመራማሪ ዶክተር በታ ጻማቶ በበኩላቸዉ ፕሮጀክቱ በዩኒቨርሲቲዉ ተደራሽ በሆኑ ሶስት ዞኖች እና ሁለት ልዩ ወረዳዎች ተፈጻሚ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ጋሞ፣ ጎፋና ኮንሶ ዞኖች እንዲሁም ደራሼና ባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች ፕሮጀክቱ የሚተገበርባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በዩኒቨርሲቲዉ ካውንስል መወሰኑንም አስረድተዋል።

የፕሮጀክቱ ዓላማዉም ተማሪዎች ራዕይ ሰንቀዉ የመማር ሃላፊነት እንዲወስዱ፣ የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ ማገዝ፣ ከፍ ሲልም በሀገር ደረጃ የተሻለ ትውልድ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ነው ብለዋል።

በተነደፈዉ ፕሮጀክት ዙሪያ የሚደረገው ጥናት በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ተጠናቆ ወደ ተግባር እንደሚገባም ዶክተር በታ ጠቁመዋል።

በዩኒቨርሲቲዉ የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ በትምህርት ቁሳቁስ፣ በስልጠና፣ በጥናትና ምርምር እያደረገ ያለው ድጋፍ መልካም መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጉቼ ሲሳይ ናቸው።

ለፕሮጀክቱ መሳካት በአካባቢው የሚገኙ የትምህርት አመራርና ህብረተሰቡን በማሳተፍ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ ከጋሞ፣ ከጎፋ እና ከኮንሶ ዞኖች፣ ከባስኬቶና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የትምህርት ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም