ለኢንተርፕራይዞች የሚሰጠው ሥልጠና ከራስ አልፎ ለአገር ልማት የሚጠቅም በመሆኑ ተመዝግበናል- ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
ለኢንተርፕራይዞች የሚሰጠው ሥልጠና ከራስ አልፎ ለአገር ልማት የሚጠቅም በመሆኑ ተመዝግበናል- ወጣቶች

አዲስ አበባ (ኢዜአ)ጥር 21/2015 ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሰጠው ሥልጠና ከራስ አልፎ ለአገር ልማት መሰረት የሚጥል መሆኑን በመረዳት ለመሰልጠን መመዝገባቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በመላው ኢትዮጵያ ባሉት 24 ዲስትሪክቶች፣ በ4ኛው ዙር የኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ሥልጠና መቐለ እና ሽሬን ጨምሮ በ25 የተለያዩ ከተሞች ምዝገባ እየተካሄደ ይገኛል።
በ4ኛው ዙር ሥልጠና ባንኩ ከ50 እስከ 60 ሺህ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾችን ለመመዝገብ ዕቅዶ እየሰራ ሲሆን ምዝገባው እስከ ዛሬ የሚቀጥል መሆኑ ታውቋል።
በሥልጠናው ለመሳተፍ ከተመዘገቡት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሰጠው ሥልጠና ከራስ አልፎ ለአገር ልማት መሰረት የሚጥል መሆኑን በመረዳት ተመዝግበናል ብለዋል።
የኢዜአ ሪፖርተር በአዲስ አበባ በተንቀሳቀሰባቸው የምዝገባ ቦታዎች በርካቶች የሥልጠናው ተጠቃሚ ለመሆን ተሰልፈው ሲመዘገቡ ተመልክቷል።
ከተመዝጋቢዎቹ መካከል ወጣት ዘለቀው አለሙና ወጣት ባንቺጊዜ አዳነ፤ የሥልጠናው ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሰጠው ሥልጠና ከራስ አልፎ ለአገር ልማት መሰረት የሚጥል መሆኑን በመረዳት ለመሰልጠን ተመዝግበናል ሲሉም ወጣቶቹ ተናግረዋል።
ሌሎች ያነጋገርናቸው ወጣት ሞገስ በየነ እና ወጣት ቃለአብ ሰለሞን፤ የአንድ ሀገር እድገት ሊረጋገጥ የሚችለው ሰርቶ በመለወጥ በመሆኑ ለዚሁ ዓላማ በሚያግዘን ሥልጠና ላይ ለመሳተፍ ተመዝግበናል ብለዋል።

እንዲህ ዓይነት ዕድሎች ከወጣቶች ተጠቃሚነት ባለፈ ለአገር ልማት ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ያብሥራ ከበደ፤ ዜጎች ከራሳቸው አልፎ ለአገራቸው የልማት ግብ ስኬት የጎላ ሚና እንዲኖራቸው አቅዶ ባንኩ የድርሻውን አበርክቶ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለ4ኛው ዙር የኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ሥልጠና ለመስጠት ከጥር 6 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በምዝገባ ላይ መሆኑ ይታወቃል።