የድሬዳዋ ነዋሪዎች ለዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ ተቀናጅተው እንደሚሰሩ አስታወቁ

ድሬዳዋ (ኢዜአ) ጥር 20/2015…የተጀመረውን ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ እና ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ተግባር ላይ ተቀናጅተው በመስራት ኃላፊነታቸው እንደሚወጡ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ።

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ተወያይተዋል።


ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የአፍረን ቀሎ አባገዳ አቶ አብዱማሊክ አህመድ እንዳሉት የኢትዮጵያ አንድነት በማፅናት ዘላቂ ሰላም እና ዕድገት ለማስመዝገብ አገራዊ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ ።


የሚፈለገውን ለውጥ እንዲመጣ በህዝቦች መካከል ሁከት እና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚጥሩ በመንግሥት መዋቅርም ሆነ በሌሎች ተቋማት ውስጥ የሚሽለኮለኩ ሀሰተኛና ሌቦችን ማስወገድ ይገባል።

መላከ አርያም ቀሲስ አእምሮ ጨመረ በበኩላቸው በድሬደዋ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ህብረ ብሔራዊ አንድነታቸውን አፅንተው ለአካባቢያቸው ብሎም ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት በአንደነት እየተጉ ናቸው ብለዋል።

በሀገር ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተካሄደው ውይይት መሠረታዊ ጉዳዮችን የሚያስጨብጥ መሆኑን ገልዋል።


እንዲሁም በቀጣይ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና የብልፅግና ከፍታ ለማረጋገጥ፣ ኃይማኖትና ፖለቲካን ተገን በማድረግ ሀገርን ለመበጥበጥ የሚሞክሩን ለህግ ለማቅረብ እየተደረገ ያለውን ርብርብ ለማጠናከር ያስችለናል ብለዋል።

ሴቶች ከማጀት እስከ አገር ለዘላቂ ሰላምና አንደነት መጠናከር መሠረታዊ ሚና እንደሚጫወቱ የገለፁት ደግሞ ወይዘሮ ሙና አብዲ ናቸው።


ውይይቱ በአገር ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ ግንዛቤ ያስጨበጠ እና ሴቶች እያበረከቱ ያለው አስተዋጽኦ ለማጠናከር ወሳኝ ይሆናል ብለዋል።

የአገርን ከፍታና የህዝብን አንድነት የማይፈልጉ አካላት እና የማህበራዊ ሚዲያ ሁከት ፈጣሪ ወሬዎችን በሰከነ መንፈስ በመረዳትና በመከላከል የተሻለች አገርን ለመፍጠር እንደሚያግዝም ተናግረዋል።

የአገር ሽማግሌው አቶ ዩሱፍ ሙሣ በበኩላቸው መንግስትና ህዝብ በየጊዜው በሀገር ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየት የጋራ መግባባት በመፈጠር ቀጣዩን የሀገር ዘላቂ ሰላም፣አንድነትና የብልፅግና ጉዞ እውን ለማድረግ መሠረታዊ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ለዚህ ዓላማ መሳካት በውይይቱ የተገነዘቡትን ለህብረተሰቡ በማሳወቅ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ እንተጋለን ብለዋል።

ውይይቱ አገር ገንቢውና ተረካቢው ወጣቱ ትውልድ አሁናዊውን የአገር መሠረታዊ ጉዞዎች እና መንግስት እያከናወናቸው የሚገኙትን ሁሉን አቀፍ ስራዎች እንዲገነዘብ ያስቻለ ነው ያለው ደግሞ ወጣት አብዱልናስር መሐመድ ነው።

መንግስት ለዘላቂ ሰላም መስፈን ያሳየው ቁርጠኝነት ወጣቱ በትምህርትና በስራ ላይ እንዲረባረብ ያስቻለው በመሆኑ የተጀመረውን የሰላም ጎዳና ለማጠናከር ወጣቱ የድርሻውን ይወጣል ብሏል።

በዚሁ " ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለብልፅግና ጉዟችን ስኬት" በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው ውይይ የአገር ሽማግሌዎች፣የኃይማኖት አባቶች፣ ዑጋዞች፣አባ ገዳዎችና የህብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም