የፀረ ሰላም ቡድኖችን ሴራ ለማምከን በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ

91

ደብረ ብርሃን(ኢዜአ) ጥር 20/2015---በአማራ ከልል ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች ፀረ ሰላም ቡድኖች በህዝብ ላይ የሚያደርሱትን ጥፋት ለማምከን በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ አጥፊዎችን በማጋለጥ የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ።

በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ሰማ ጥሩነህ እንዳሉት፣ አሸባሪው የሸኔ ቡድን በተደጋጋሚ የህዝብን ሰላም እየነሳ ይገኛል።

ሰሞኑን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች አዋሳኝ ወረዳዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልጸው፣ "ቡድኑና ግብር አበሮቹ በህዝብ እና በሀገር ላይ የሚፈጽሙትን የጥፋት ተግባር በጋራ መከላከል ይገባል" ብለዋል።

ሀገራዊ የለውጥ ጉዞን ለማደናቀፍ ጽንፈኛ ቡድኖች አንዴ በብሔር ሌላ ጊዜ በሃይማኖት ሽፋን ችግር ለመፍጠር ቢንቀሳቀሱም በቅንጅት በሚወሰድ እርማጃ ህልማቸው እየመከነ መሆኑን አመልክተዋል።

"ለዘመናት በደምና ሥጋ የተጋመዱ ህዝቦችን ለመነጣጠልና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚደረገው ሴራም መቼም ቢሆን አይሳካላቸውም" ሲሉም ዶክተር ሰማ ገልፀዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎችም የተረጋጋ ሰላም ለማስፋን እየተወሰደ ባለው እርምጃ ሸኔን እና ጽንፈኛ ቡድኖችን አጋልጠው በመስጠት የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ በበኩላቸው፣ "የሸኔ ሽብር ቡድን የጥፋት ሴራ በፀጥታ መዋቅሩና በፖለቲካ አመራሩ የተቀናጀ ጥረት ለመቀልበስ ተችሏል" ብለዋል።

ጽንፈኛ ቡድኑ በአብሮነት፣ በሰላምና በፍቅር የኖረውን ህዝብ በማጋጨት ሀገርን ለማፍረስ ያለመ ጥቃት ሰሞኑን መፈጸሙን ተናግረዋል።

እውነታው ይሄ ሆኖ እያለ አንዳንድ የፖለቲካ ነጋዴዎች የአማራ እና የኦሮሞ ህዝቦች ብሎም የሃይማኖት ግጭት አደርገው የሚያናፈሱት ወሬ መሰረተ ቢስ መሆኑን አቶ ግርማ ገልጸዋል።

"በአካባቢው ከሚንቀሳቀሰው የሸኔ ቡድን ጋር የኦሮሞ ህዝብ ቁርኝት የለውም" ያሉት አቶ ግርማ፣ ማህበረሰቡ ጽንፈኛ ቡድኑን አጋልጦ በመስጠት እንዲተባበር ጠይቀዋል።

ህብረተሰቡም ከሀሰተኛ መረጃ ሰጪዎች እራሱን መጠበቅ እንዳለበት ጠቁመው፣ "ሰሞኑን በአካባቢው የተፈፀመው ወንጀልና የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ ወደሥራ ገብቷል" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ያለውን አንፃራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ከመላከያ ሠራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከአማራ ልዩ ሀይል እና ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አቶ ግርማ አስታውቀዋል።

በሰላም እጦቱ በአካባቢው ተቋርጦ የነበረው የህዝብ ማመላለሻና የጭነት ተሽከርካሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ከነገ ጥር 21 ቀን 2015 ጀምሮ እንደሚጀመርም አስታውቀዋል።

"በእዚሁ የጸጥታ ችግር በሁለቱ ዞኖች በሚገኙ ወረዳዎች ተቋርጦ የነበረው የመንግስት ሥራና የንግድ እንቅስቃሴም ከነገ በስቲያ ሰኞ ጀምሮ ይጀመራል" ሲሉም አክለዋል።

የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉም በሃላፊነት መንፈስ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አቶ ግርማ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም