ልማትን ለማፋጠን እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ጠንካራ የዜጎችን ተሳትፎ ይጠይቃል

202

ሀዋሳ (ኢዜአ) ጥር 20/2015 ልማትን ለማፋጠን እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እየተደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ጥረት ስኬት ጠንካራ የዜጎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር አብዲዋስ አብዱላሂ ገለጹ።

በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አብይ ትኩረቱን ያደረገ ህዝባዊ ውይይት ዛሬ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።

ዶክተር አብዲዋስ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት መንግሥት የአንድን ሀገር ልማትና ዕድገት ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የህዝብ አበርክቶ ትልቁን ድርሻ ይይዛል።

በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተደረገ ባለው ጥረት ውስጥ የህዝቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ህዝቡ በሀገሩ ጉዳይ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ እንዲኖረው በማድረግ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ እየተደረገ ላለው ርብርብ ስኬት በተቀናጀ መንገድ መተጋገዝ እንደሚገባም አመልክተዋል።

በተለይ ለተጀመሩ የሰላም፣ የልማትና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሥራዎች ስኬት ጠንካራ የወንድማማችነትና አንድነት መንፈስ እንደሚያስፈልግ ዶክተር አብዲዋስ ገልጸዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው ሀገራችን ባለፉት ጊዜያት ያጋጠሟትን ጋሬጣዎች በህዝቡ የተባበረ ክንድ መመከት መቻሉን ገልጸዋል።

የቀጣይ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ምስረታ፣ ፈጣን ልማትና ዕድገትን ማረጋገጥ እንዲሁም መልካም አስተዳደርን ማስፈንና የተጀመሩ ስኬታማ የለውጥ ስራዎችን ከግብ እንዲደርሱ ማድረግ የሀገሪቱን ሕዝቦች ቁርጠኛ አቋም የሚሹ ጉዳይ ናቸው ብለዋል።

ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይን መነሻ ተደርጎ በተካሄደ የውይይት መድረክ የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ ለማጠናከር የሚያስችሉ የጋራ አቋምና ስምምነት ላይ ተደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም