የቢሾፍቱ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ከጸጥታ፣ ሙስናና ሌብነት እንዲሁም ከኑሮ ውድነት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
የቢሾፍቱ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ከጸጥታ፣ ሙስናና ሌብነት እንዲሁም ከኑሮ ውድነት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠየቁ

አዲስ አበባ ( ኢዜአ) ጥር 20/2015 -- የቢሾፍቱ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ከጸጥታ፣ ሙስናና ሌብነት እንዲሁም ከኑሮ ውድነት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠየቁ።
ችግሮቹን በዘላቂነት ለማስወገድ በየአካባቢው ያሉ ችግር ፈጣሪዎችን ለሕግ አሳልፎ መስጠት እንደሚገባም ተገልጿል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ከቢሾፍቱ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ከከተማዋ የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የቢሾፍቱ ከተማዋንና አካባቢዋን ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው የሰላም እጦት መፍትሔ ሊያገኝ ይገባል ብለዋል።
በዚህ የሰላም እጦት ምክንያት የክልሉ ሕዝብ በተለይም በአሸባሪው ሸኔ ምክንያት የተለያዩ ችግሮች ውስጥ ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል።
በተለይም በገጠር የሚኖረው ሕዝብ በሽብር ቡድኑ ምክንያት መደበኛ የግብርና ስራውን ለማከናወን ጭምር እየተቸገረ መሆኑን አንስተዋል።
ተሳታፊዎቹ አሁንም በሌብነት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች መበራከት ምክንያት አገልግሎት ማግኘት ከባድ መሆኑን አንስተው፤ ይህም እልባት ሊያገኝ ይገባል ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ከመቅረፍና የኑሮ ውድነት ከማረጋጋት አንጻር መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግሥት በርካታ የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎችን ማከናወኑን የውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
በሁሉም ዘርፍ የተገኘው አበረታች ውጤት የበለጠ እንዲጠናከር ከመንግሥት ጎን ሆነው የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ዓለማየሁ አሰፋ በበኩላቸው የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በተለይም በከተማዋ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የጀመረው ስራ የበለጠ ውጤት እንዲያመጣ ነዋሪው ማገዝ አለበት ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ሌብነትና ብልሹ አሰራር ላይ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ገልጸው ነዋሪውም ይህን የተጀመረ ጥረት እንዲያግዝ ጠይቀዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የታየውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ አካላት መኖራቸውን የገለጹት ደግሞ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ ናቸው።

ሚኒስትሩ እነዚህ አካላት የተለያየ ማንነትን እየተላበሱ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨትና ግጭት ለማባባስ እየሰሩ ነው ብለዋል።
ጽንፈኞች ለየትኛውም ወገን እንደማይጠቅሙ ሊታወቅ ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ ሕዝቡ ከመንግስት ጎን በመሆን ጽንፈኝነትን በፅናት ሊታገል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በኦሮሚያ ክልል አንድንድ አካባቢዎች የፀጥታ ችግር እየፈጠረ የሚገኘው አሸባሪው ሸኔም በዋናነት ተጎጂ ያደረገው የኦሮሞን ሕዝብ ነው ብለዋል።
መንግሥት ከምን ጊዜውም በላይ ለሰላም ያለው ቁርጠኝነት ትልቅ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ለገሰ በተለያየ ምክንያት የሽብር ቡድኑን የተቀላቀሉ ወጣቶች ወደ ሰላም እንዲመለሱ አሳስበዋል።
ይህ እንዲሳካ ደግሞ አባገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች ወጣቶቹ ወደ ሰላማዊና መደበኛ ኑሯቸው እንዲመለሱ እያደረጉት ያለውን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ዛሬ መካሄዱ ይታወቃል።