ጸረ-ሰላም ሃይሎች የሚፈጥሩትን የጸጥታ ችግር በመፍታት የተገኘውን ለውጥ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል

ቻግኒ (ኢዜአ) ጥር 20/2015….በአማራና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የግጭት ነጋዴዎች ይፈጥሩት የነበረውን የሰላምና የፀጥታ ችግር በመፍታት የተገኘውን ለውጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የሰላም ሚኒስቴር አስገነዘበ።

የሰላም ሚኒስቴር ከአማራ ክልል ጋር በመተባበር በሁለቱ ክልሎች የተገኘውን መልካም ልምድ አጠናክሮ ማስቀጠል የሚያስችል ጉባኤ በቻግኒ ከተማ ተካሄዷል።

የሰላም ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ጌታዋ ደስታው በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካካባቢዎች እምቅ የመልማት አቅም ያለው ነው።

በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገነባበት አካባቢና የጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት የሚገኝበት አካባቢና መመላለሻ መንገድ መሆኑን ገልፀዋል።

በተጨማሪም ሰፋፊ የግብርና ኢንቨስትመንት የሚካሄድበት በመሆኑም ለኢንዱስትሪ፣ ለቱሪዝምና ለሌሎች ልማቶች ተመራጭ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ካለፉት ቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉ የግጭት ነጋዴዎች በፈጠሩት ችግር ንጸሃን ዜጎች መገደላቸውን፤መፈናቀላቸውን፤ ሀብት ንብረት መውደሙን አስታውሰዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሁለቱ ክልሎች አመራሮች፣ የፌዴራልና የክልል የፀጥታ ሃይሎች እንዲሁም ህዝቡ በጋራ ባደረጉት ጥረት አካባቢው ወደ ቀድሞው ሰላሙ መመለሱን ተናግረዋል።

እየታየ ያለው ሰላም፣ የህዝብ ለህዝብ መቀራረብና አብሮነት በአርዓያነት የሚጠቀስ ስኬት የተመዘገበበት ነው ብለዋል።

የጉባኤው ዋና ዓላማ የተገኘውን መልካም ተሞክሮ አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በጋራ መክሮ ማስተካከልና የተጀመረውን የጋራ የመልማት እሳቤ ዳር ማድረስ እንደሆነም ተናግረዋል።

በአማራ ክልል የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንግዳ ዳኘው እንዳሉት በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረው ችግር እጅግ አሳዛኝ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከፌዴራል እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በተደረገው የጋራ ጥረት አሁን የአካባቢውን ልማትና ሰላም በጋራ ማረጋገጥ የተቻለበት ደረጃ ላይ መደረሱን አስረድተዋል።

በጉባኤው የፌዴራልና የክልል የሥራ ሃላፊዎች የሁለቱ ክልሎች የአዋሳኝ አካባቢዎች የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት፣ አባቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም