ዕድሮች የሕብረተሰቡን አብሮነት የሚያስጠብቁ ተግባራትን ለማስቀጠል ይሰራሉ

166
አዲስ አበባ  መስከረም 24/2011 የሕብረተሰቡን አብሮነት የሚያስጠብቁ ተግባራትን ለማስቀጠል እንደሚሰሩ በአዲስ አበባ የሚገኙ የዕድር ምክር ቤት ሀላፊዎች ገለጹ። ቀብር ከማስፈጸም ያለፈ ተሳትፎ ያልነበራቸው እድሮች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መተዳደሪያ ደንቦቻቸውን በማሻሻል በልማት ስራዎችና በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ ጀምረዋል። እድሮች ሲመሰረቱ ከሀይማኖት፣ ከብሄር፣ ከፖለቲካና ሌሎች ጉዳዮች ነጻ ሆነው በመሆኑ የሁሉንም ሕብረተሰብ የጋራ ሀሳብና እሴት ይዘው እየሰሩ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የዕድር ምክር ቤት ሀላፊዎች ገልጸዋል። ከመደበኛ ስብሰባዎቻቸው በተጨማሪ በተለያዩ ማህበራዊ ክስተቶችና በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ስለ ሰላምና አብሮነት እንደሚመክሩ በማውሳት ይህም የዕድሮች አንዱ ሀላፊነት በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የዕድር ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሶሪ ዲባባ የአገሪቷን አንድነት ማጠናከር የዕድሮች አጀንዳ በመሆኑ ይህንኑ ለማህበረሰቡ የማስገንዘብ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው ያስረዱት። የአራዳ ክፍለ ከተማ እድሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ስዩም በቀለ ህብረተሰቡ አብሮነቱን እንዲያስጠብቅ በውይይቶችና በማህበራዊ ጉዳዮች በሚገናኙባቸው አጋጣሚዎች እንደሚመክሩ ነው የተናገሩት። ዕድሮች በአባላት ዘንድ ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም አገሪቷ የጀመረችውን የመደመር ጎዞ ለማስቀጠል ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ የገለጹት ደግሞ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እድሮች ምክር ቤት አባል አቶ ለማ ዲሬሳ ናቸው። የአዲስ አበባ የዕድሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ታምራት ገብረማርያምም በአገሪቷ እየታዩ ያሉ ተስፋ ሰጪ ለውጦች እንዲቀጥሉ ድጋፍ ማድረግ የእድሮች ትልቁ ስራ ነው ይላሉ። ከመጪው ጥቅምት ጀምሮ በሚካሄዱ ከተማ አቀፍ መድረኮች ሰለ ሰላምና አንድነት ንቅናቄ ለመፍጠር እንደሚሰሩም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም