በሀገሪቱ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ግብር ከፋዮች ግብርን በታማኝነትና በወቅቱ ሊከፍሉ ይገባል- የገቢዎች ሚኒስቴር

101

ሀዋሳ ፤ ጥር 20 ቀን 2015 (ኢዜአ)፡- በሀገሪቱ ቁጠባና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እንዲቻል ግብር ከፋዮች ግብርን ሳይሰውሩ በታማኝነትና በወቅቱ ሊከፍሉ እንደሚገባ የገቢዎች ሚኒስቴር አሳሰበ።

በገቢዎች ሚኒስቴር የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ባለፈው በጀት ዓመት በህግ ተገዥነትና በክፍያ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ 24 ምስጉን ግብር ከፋዮች ዛሬ በሀዋሳ የእውቅና አስጣጥ መርሃ ግብር አካሂዷል።

በስነ- ስርዓቱ ላይ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ሥርዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ቱሉ ባደረጉት ንግግር፤ ግብር የሀገሪቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የምናሳልጥበትና ግብር ከፋዩም ሀገሩን መውደዱን የሚያረጋግጥበት ነው ብለዋል።

ግብር ገቢን ለማግኘት የሚሰበሰብ ብቻ ሳይሆን የተመጣጠነ የሃብት ክፍፍል እንዲኖርና ቁጠባና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ግብር ከፋዮች ግብርን ሳይሰውሩ በታማኝነትና በወቅቱ ሊከፍሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳመለከቱት፤ ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ገቢን ሰብስቦ የፋይናንስ ጉድለቱን በመሙላት እያደገ የመጣውን የህብረተሰብ የልማት ፍላጎት ለመመለስ ግብር ከፋዮችና ባለድርሻ አካላት የበለጠ መረባረብ ይጠበቅባቸዋል።

በሀገሪቱ የተወሰኑ ግብር ከፋዮች አሁንም በህገወጥ ተግባር ተሰማርተው ይገኛሉ ያሉት ደግሞ በሚኒስቴሩ የታክስ ጉዳዮች ትምህርት ዳይሬክተር አቶ በፍርዱ መሠረት ናቸው።

ይህንን ለማስተካከል ግብር ከፋዮች በህገወጥ ተግባር ላይ ተሳታፊ እንዳይሆኑ በማስተማርና በመደገፍ ወደ ህጋዊ ስርዓቱ እንዲገቡ አበክረው እየሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በሚኒስቴሩ የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ታደለ እንዳስታወቁት፤ ዛሬ እውቅና ከተሰጣቸው መካከል አምስቱ በገቢዎች ሚኒስቴርና ቀሪዎቹ ደግሞ በቅርንጫፉ ደረጃ ነው።

እውቅና የተሰጣቸውም በ2014 በጀት ዓመት ከ3 ሚሊዮን እስከ 607 ሚሊዮን ብር በላይ ታክስን በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል የላቀ አፈጻጸም ያስመዘገቡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

አሁን ላይ አብዛኛው ግብር ከፋይ ግብርን በአጭር ቀን በንቅናቄ የመክፈል ባህል እያዳበረ ነው ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ እውቅና መስጠቱ ግብር ከፋዮችን ለማበረታትና ለሌሎች አርአያ እንዲሆኑ ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።

ቅርንጫፉ ባለፉት ስድስት ወራት 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉንም ተናግረዋል።

እውቅና ከተሰጣቸው ምስጉን ግብር ከፋዮች መካከል ወይዘሮ ይርጋለም አሰፋ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ግብር መክፈል በሀገር እድገት ላይ የራስን አሻራ ማሳረፍና የመጪውን ትውልድ እጣ ፈንታ መወሰን ስለሆነ የሚጠበቅብኝን ግብር በወቅቱ እየተወጣሁ ነው ብለዋል።

የገቢዎች ሚኒስቴር ለሰጣቸው እውቅና ምስጋና አቅርበዋል።

ሌላው እውቅና የተሰጣቸው ግብር ከፋይ ዶክተር ግርማ አባቢ ፤ ግብር መክፈል ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ምሰሶ በመሆኑ ሁሉም ወገን ካለማንም ጉትጎታ በኃላፊነት ስሜት የሚጠበቅበትን ሊወጣ ይገባል ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

የገቢ ሰብሳቢ ተቋም አሰራር በየጊዜው እየተሻሻለ መጥቷል ያሉት ዶክተር ግርማ፤ የግብር ከፋዩን ማህበረሰብ ግንዛቤ ለማሳደግ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም