በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር መረጋጋቱን የዞኖቹ አስተዳዳሪዎች ገለፁ

132

ደብረ ብርሃን(ኢዜአ)ጥር 20/ 2015 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች ሰሞኑን በፅንፈኛ ቡድኖች ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር መረጋጋቱን የዞኖቹ አስተዳዳሪዎች ገለፁ።

በአካባቢው ሰላሙን በዘላቂነት ማረጋጋጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የመከላከያ፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የአማራ ልዩ ሃይል አመራሮች እና የአስተዳደሮቹ አመራሮች በአጣየ ከተማ መክረዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ ዓለማየሁ እንደገለጹት፣ ውስጣዊ ችግሮችን እርስ በእርስ ተወያይቶ በመፍታት ለዘላቂ ሰላም በጋራ እየተሰራ ነው።

የፀረ ሰላም ቡድኖችን ተደጋጋሚ የጥፋት ሴራ ከምንጩ ለማድረቅ በአካባቢው ከተመደቡት የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ እና የአማራ ልዩ ሃይል ጋር በቅንጀት በመስራት ጽንፈኛ ቡድኖችን ለህግ ለማቅረብ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

ለሰላም ጠንቅ የሆኑ በእነዚህ ቡድኖች ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት በማረጋገጥ የህዝቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ወደነበረበት ለመመለስ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አቶ መካሻ አመልክተዋል።

በቅንጅት እየተከናወነ ባለው የሰላም ማስከበር ሥራ በአሁኑ ወቅት አካባቢው ወደ መረጋጋት እየተመለሰ መሆኑን ገልጸው፣ "ሰላሙ በተሟላ ሁኔታ እንዲረጋግጠም የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ" ብለዋል።

"በአንዳንድ የብዙሀን መገናኛዎች 'አጣየ ከተማ ወድማለች' በሚል የተሰራጨው ወሬ ሀሰተኛ ነው" ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፣ ህብረተሰቡ አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅና ፀረ-ሰላም ቡድኖችን በመታገል ለመንግስት የፀጥታ ሃይሎች እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በአካባቢው የተከሰተው የፀጥታ መታወክ ጽንፈኞች አካባቢውን በማተራመስ አገርን ለማፍረስ በማለም የፈጠሩት እኩይ ሴራ ነው።

የአሸባሪው ሸኔ ፅንፈኛ ቡድኖች ከፍተኛ የጥፋት ተልዕኮ አልመው ቢነሱም በመከላከያ ሠራዊት፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በአማራ ልዩ ሀይልና በህብረተሰቡ ትብብር የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በቅንጅት በተደረገው እንቅሰቃሴ አሁን ላይ በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም መስፈኑንና የተጀመሩ ሰላምን የማምጣት ሥራዎች የበለጠ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

"ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ህብረተሰቡን ያሳተፈ ተከታታይ የሰላም መድረኮች በማካሄድ ፀረ-ሰላም ቡድኖችን ከተሰገሰጉበት መንጥሮ ለህግ ለማቅረብ ይሰራል" ብለዋል።

የአካባቢው ህዝብም በውስጡ ተሸሽገው በመሳሪያ ንግድ እና የሀሰት ወሬ በመንዛት ህዝብን ሲያሸብሩና ሲያስገድሉ የነበሩ ወንጀለኞችን አጋልጦ በመስጠት የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ዋና አስተዳዳሪው እንዳሉት ህዝቡ በአንዳንድ የብዙሀን መገናኛዎች በሚናፈሱ ወሬዎች ሳይረበሽ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ተገቶ መስራት ይኖርበታል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት ባለድርሻ አካላት የአካባቢው ሰላም በዘላቂነት በሚጠበቅበት ሁኔታ ላይ በመምከር አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ተመላክቷል።

በዚህም የአካባቢውን ሰላም ከሚያስከብረው የተቀናጀ የፀጥታ አካል እውቅና ውጪ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም