ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ግንባታ የሚውል 10 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለብ ደጋፊዎች ማህበር አስረከቡ

245


አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 20/2015 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ለስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ግንባታ የሚውል ቦታ 10 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለብ ደጋፊዎች ማህበር ዛሬ አስረክበዋል።

ማህበሩ የተረከበው መሬት የረጅም ጊዜ ጥያቄ የነበረ መሆኑን የከንቲባ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ደጋፊዎች ጋር በቅርቡ ባካሄዱት ወቅት ደጋፊዎቹ ካነሷቸው በርካታ ጥያቄዎች መካከል አንደኛው የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎችን የማስፋፋት ጥያቄ እንደነበር ገልጿል።

ከንቲባዋ ከጥያቄዎቹ አንዱ የሆነው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ደጋፊዎች ማህበር የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ በቦታው ላይ የነበሩ የተለያዩ ሕገወጥ ደላሎችንና የይገባኛል ጥያቄዎችን በመፍታት ለማህበሩ ማስረከባቸውን አመልክቷል።

ከንቲባ አዳነች “የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ ቦታ ብቻ ሳይሆን ሀገርንም የምንገነባው ተባብረን ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

“በከተማው የተለያዩ የልማት ስራዎቻችን ከሕገወጥ ደላሎች ጋር ትንቅንቅ በማድረግ የልማት እንቅፋቶችን እየተጋፈጥን ነው ስራዎችን እየሰራን ያለነው” ብለዋል፡፡

በመሆኑም ሕብረተሰቡ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በየአካባቢው ለልማት እንቅፋት የሚሆኑ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን በመግታት ሚናውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች ርክክብ የተደረገበት ቦታ በፍጥነት ወደ ልማት እንዲገባ አቅጣጫ መስጠታቸውንና የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ቦርድ በፍጥነት ግንባታውን እንደሚያስጀምር ቃል መግባቱ ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም