ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በመመልከታችን ለበለጠ ድጋፍ እንድንነሳሳ ወኔ ፈጥሮብናል - ግድቡን የጎበኙ የዳያስፖራ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በመመልከታችን ለበለጠ ድጋፍ እንድንነሳሳ ወኔ ፈጥሮብናል - ግድቡን የጎበኙ የዳያስፖራ አባላት

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 19/2015 ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በመመልከታችን ለበለጠ ድጋፍ እንድንነሳሳ ወኔ ፈጥሮብናል ሲሉ የግድቡን የጎበኙ የዳያስፖራ አባላት ተናገሩ።
በመላው ክፍላተ-ዓለማት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የዳያስፖራ አባላቱ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግንባታን ዛሬ ጎብኝተዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የዳያስፖራ አባላት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በራሳችን ሀብት የተገነባ፣ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማማ የሚወስድ፣ ለትውልድ የሚሻገርና የኩራት ምንጭ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ግድቡን በአካል መመልከታቸው የተለየ ስሜት እንደፈጠረባቸው ጠቅሰው፤ "ግድቡ በኢትዮጵያ አቅም ብቻ መገንባቱ ትልቅ ኩራትና ልብን የሚያሞቅ ወኔ ፈጥሮብናል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በአስቸጋሪ የአየር ጠባይ ውስጥ ሆነው ለ24 ሰዓት ግድቡን ዳር ለማድረስ እየተጉ ላሉ የግድቡ ሰራተኞችን አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ይህም ለግድቡ የበለጠ ድጋፍ ለማድረግ መነሳሳት እንደፈጠረባቸውም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በገጠማት ሰላም ዕጦት ሳቢያ ዳያስፖራው በአብዛኛው በሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት ላይ ትኩረት በማድረጉ ለግድቡ ሲደረግ የነበረው ድጋፍ ተቀዛቅዞ መቆየቱን የዳያስፖራ አባላቱ ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ የሰላም ስምምነቱ ዳያስፖራው ፊቱን ወደ ልማት ፕሮጀክቶች እንዲያዞር እና ግድቡን ወደ ፍጻሜ ለማድረስ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
በመላው ክፍላተ-ዓለማት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ያለምንም ልዩነት ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወደ ፕሮጀክቱ በአካል በመምጣት መጎብኘት፣ የገጽታ ግንባታ ሥራዎችን ማከናወንም ይጠበቃልም ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ በበኩላቸው፤ ግድቡን የጎበኙ ዳያስፖራ አባላት ድጋፋቸው ፍሬ ማፍራቱን ያዩበትና ለበለጠ ድጋፍ መነሳሳት የፈጠሩበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የዳያስፖራ አደረጃጀቶች የሚያደርጉትን የድጋፍ ማሰባሰብ ስራ ይበልጥ ለማሳለጥ እንደሚያግዝም አመልክተዋል።
ዳያስፖራው በጦርነት ወቅት አገር ለማዳንና የተጎዱ ወገኖችን የመደገፍ ተሳትፎ ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰው፤ አሁን ላይ በተቀናጀ መልኩ የልማት ፕሮጀክቶችን እንዲደግፍ የሚያደርጉ አሰራሮች እንደሚዘረጉም ጠቁመዋል።
ከዚህ አኳያ አገልግሎቱ በየአገራቱ ከሚገኙ የዳያስፖራ አደረጃጀቶችና ኤምባሲዎች ጋር በመተባበር ሀብት የማሰባሰብ ስራዎችን የማጎልበት ኃላፊነቱን ይወጣል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ።
የተለያዩ የዳያስፖራ አደራጃጀቶች ለአገራቸው ባደረጉት ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ ሀገር አቀፍ ዕውቅና እና ሽልማት ትናንት በተካሄደ መርሐግብር እንደተበረከተላቸው የሚታወስ ነው።