የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የተጀመሩ የመልሶ ማቋቋም ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - የመከላከያ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የተጀመሩ የመልሶ ማቋቋም ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - የመከላከያ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ (ኢዜአ)ጥር 19/2015 በፌዴራል መንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የተጀመሩ የመልሶ ማቋቋም ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የመከላከያ ሚኒስቴር ገለጸ።
የመከላከያ ሚኒስቴር የሰላም ስምምነት አተገባበሩን አስመልክቶ አዲስ አበባ ለሚገኙ የተለያዩ አገራት ወታደራዊ አታሼዎች ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
ማብራሪያውን የሰጡት በሚኒስቴሩ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዳይሬክተር ጀነራል ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ፤ ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ መንግስት በትግራይ ክልል የተለያዩ አገልግሎቶችን በፍጥነት ማስጀመሩን ገልጸዋል፡፡

የዛሬው መድረክም በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ አገራት አታሼዎች መንግስት ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ያለውን ቁርጠኝነት እንዲገነዘቡ ማድረግን ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ይህም በጉዳዩ ላይ ትክክለኛ መረጃ እንዲኖራቸው ያስችላል ነው ያሉት፡፡
ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ መንግስት በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ ከዚህ አኳያ በትግራይ ክልል መሰረተ ልማቶች በፍጥነት ወደ አገልግሎት እንዲገቡ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የአውሮፕላን በረራ፣ የባንክ እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች በፍጥነት መጀመራቸው ጠቁመዋል፡፡
መንግስት ወደ ትግራይ ክልል ያልተቋረጠ ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን ማድረጉንና ሌሎች የመልሶ መቋቋም ስራዎችን በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡
ወታደራዊ አታሼዎች በበኩላቸው የሰላም ስምምነቱ አተገባበር በጥሩ ሂደት ላይ መሆኑን እንደተገነዘቡ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት እያከናወነ ያለውን ሰራ አድንቀዋል፡፡
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የአውሮፕላን በረራ፣ የባንክ እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች በፍጥነት እንዲጀመሩ ማድረጉ ይታወሳል፡፡