የአዲስ አበባ ስታዲየም ሁለተኛ ምዕራፍ የዕድሳት ሥራ ለማከናወን 150 ሚሊዮን ብር ተመድቧል- የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

167

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 15/2015 የአዲስ አበባ ስታዲየም ሁለተኛ ምዕራፍ የዕድሳት ሥራ ለማከናወን 150 ሚሊዮን ብር መመደቡን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ጨዋታዎችን በብቸኝነት ሲያስተናግድ የነበረው የአዲስ አበባ ስታዲየም በካፍ እና ፊፋ የተቀመጠውን መመዘኛ ባለማሟላቱ ጨዋታዎችን እንዳያስተናግድ መታገዱ ይታወቃል።

ይህንን ተከትሎ ስታዲየሙን ወደ ስራ ለማስገባት በሰኔ 2013 ዓ.ም ጨረታ ወጥቶ የእድሳት ሥራ መጀመሩ ይታወሳል።

በባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንዳሉት ለስፖርት መስፋፋት የጀርባ አጥንት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ግንባር ቀደሙ የስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታ ነው።

መንግስትም ይህን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ከጥርጊያ ሜዳ አንስቶ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞችን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን እገዛ እያደረገ ይገኛል፡፡

May be an image of grass

ይሁን እንጂ የሚሰሩ ስታዲየሞች በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅና የጥራት ችግር እንደሚታይባቸው ነው የገለጹት።

ችግሩን ለመፍታትም በፌደራል መንግስት እገዛ የአዲስ አበባ ስታዲየም ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እድሳት እየተደረገለት እንደሚገኝ አምባሳደር መስፍን ተናግረዋል፡፡

የስታዲዬሙ ዕድሳት የሚከናወነው የካፍ መመዘኛ መስፈርትን መሰረት በማድረግ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ እንዲችል ተደርጎ ነው።

የመጀመሪያው ምዕራፍ ዕድሳት የአንድ አመት ጊዜ ቀጠሮ ተይዞለት በ39 ሚሊዮን ብር ወጪ በሰኔ 2013 ዓ.ም ቢጀመርም በተለያየ ምክንያት ከታቀደው ጊዜ የዘገየው የስታዲየሙ ዕድሳት አሁን ላይ የመጫወቻ ሜዳ ሳር ተከላው መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በመጀመሪያው ምዕራፍ የሚሰሩ የመልበሻና የመታጠቢያ ክፍሎች እድሳትን ጨምሮ የስታዲሙ ግንባታ አሁን ላይ 97 በመቶ ስራው መጠናቀቁን ነው የገለጹት።

ስታዲሙ ለበርካታ ዓመታት ከእግር ኳሱ ውጭ ተደራራቢ የሆኑ በርካታ መርሃ ግብሮች ሲያስተናገድ በመቆየቱ በከፍተኛ ደረጃ መጎዳቱን አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ የሁለተኛውን ምዕራፍ ዕድሳት ለማከናወን ጨረታ መውጣቱን በመግለጽ ጨረታው እንደተጠናቀቀ ከአሸናፊው ድርጀት ጋር ውል በመዋዋል ስራው በፍጥነት እንደሚጀመር ነው የገለጹት።

መንግስት ለሁለተኛው ምዕራፍ የዕድሳት ስራ 150 ሚሊዮን ብር መመደቡንም ጠቁመዋል።

በፌደራል መንግስቱ ከሚሰሩ ስታዲየሞች በተጨማሪ በክልሎች የሚሰሩና በጅምር ያሉ ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ስታዲየም ለስፖርታዊ ክንውኖች እንዲሆን የተደረገውና የስታዲየም መልክ ኖሮት እንዲገነባ መሰረተ ድንጋይ የተቀመጠለት ጥቅምት 23 ቀን 1940 ዓ/ም መሆኑ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም