የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ አባላት ለችግረኛ የህብረተሰብ ክፍሎች የቤትና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ

59
አዳማ /ነገሌ መስከረም 24/2011 የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ በአዳማ ከተማ ጆጎ ቀበሌ በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች አደረገ ። የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ኮማንደር ጌታቸው ኢታና  በድጋፍ ስነ ስርአቱ ላይ እንደገለፁት ኮሌጁ ከሚሰጠው ስልጠና ጎን ለጎን በማህበራዊና ሰብዓዊ ልማት በመሳተፍ ህዝባዊ ወገንተኝነትን የማረጋገጥ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ። "የኮሌጁ ፖሊሶችና ዕጩ መኮንኖችም አጋርነታቸውን ለመግለፅ በአካባቢው በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ ድጋፎች አበርክተዋል" ብለዋል። ለህብረተሰብ ክፍሎቹ ከተደረጉት ድጋፎች መካከል ባለቤቶቻቸውን በተለያዩ ምክንያት በሞት ለተነጠቁና 17 የቤተሰብ አባላትን ለሚያስተዳድሩ ሦስት ሴቶች በነፍስ ወከፍ የመኖሪያ ቤቶች የተበረከተላቸው መሆኑን ተናግረዋል ። እንዲሁም ለ40 ችግረኛ ህፃናትና ቤተሰቦቻቸው ፍራሽ፣ ብርድ ልብስና አንሶላን ጨምሮ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል ። ድጋፍ ከተደረገላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል በኤች አይ ቪ ኤድስ፣ በትራፊክ አደጋና በሌሎች ምክንያቶች ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ህፃናት፣ አቅመ ደካማ አረጋዊያንንና ሰርተው መብላት የማይችሉ የአካል ጉዳተኞች ይገኙበታል። የኮሌጁ ፖሊሶችና መኮንኖቹ ለህብረተሰቡ ያበረከቷቸው ቁሳቁሶች ከ90 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል ። ባለፈው ዓመትም 200 ሺህ ብር የሚገመት ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ኮማንደሩ አስታውቀዋል ። ድጋፍ ከተደረገላቸው ነዋሪዎች መካከል የጆጎ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ተናኘ መኮሪያ በሰጡት አስተያየት  ባለቤታቸው በሞት ከተለያቸው ጊዜ ጀምሮ በችግር ውስጥ ሆነው ልጆቻቸውን በማሳደግ ላይ መሆናቸውን ቆይተዋል። የፖሊስ ሠራዊት አባላቱ ገንብተው ያስረከቧቸው መኖሪያቤት ከነበረባቸው የመጠለያ ችግር የሚያላቅቃቸው በመሆኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ። ወይዘሮ በሻዱ ዳዲ በበኩላቸው ባለቤታቸው በትራፊክ አደጋ ህይወታቸው ማለፉን ጠቅሰው ይኖሩበት የነበረው የሳር ጎጆ በተደረገላቸው ድጋፍ በቆርቆሮ ቤት በመለወጡ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል ። ልጆቻቸውም የሌሊት ልብስና የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማግኘታቸውን ተናግረዋል ። በተመሳሳይ የጉጂ ዞን ፖሊስ አባላት በነገሌ ከተማ ወላጆቻቸውን በሞት ላጡና ረዳት ለሌላቸው ህጻናት ለትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ግዥ የሚውል 19 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ጉሳዬ ከበደ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም