የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አገራዊ ተልዕኮዎችን በተሻለ ብቃት ለመፈጸም የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ማተኮር አለበት - ምክር ቤቱ

177

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 19/2015 የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አገራዊ ተልዕኮዎችን በተሻለ ብቃት ለመፈጸም የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ማተኮር እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባ ሸጎሌ እያካሄደ ያለውን ማስፋፊያ ግንባታ ጎብኝተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በአስር ሄክታር መሬት ላይ እየተገነባ ያለውን ስቱዲዮዎች፣ የሕንጻ ግንባታ እንዲሁም የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች እንዲሁም በ8ሺህ 500 ካሬ መሬት ላይ ያረፈው ሰው ሰራሽ ኃይቅም የጉብኝቱ አካል ነበር።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍሰሃ ይታገሱ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ተቋሙ እያከናወናቸው በሚገኙ የለውጥ ሥራዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላም አባላቱ ተቋሙ ተወዳዳሪ ለመሆንና አገራዊ ተልዕኮዎችን በብቃት መወጣት እንዲችል ሊስተካከሉ ይገባል ባሉት ጉዳዮች ላይ ሃሳብ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የምክር ቤቱ የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ እንደገለጹት፤ ኮርፖሬሽኑ አገራዊ ተልዕኮዎችን በተሻለ ብቃት ለመፈጸም የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ማተኮር አለበት።

በተለይም ተደራሽነት ላይ ውስንነት መኖሩን ጠቁመው በተለያዩ ቋንቋዎች በማሰራጨት የአገልግሎት አድማሱን ማስፋት ይገባዋል ሲሉ አመልክተዋል።

የሚዲያው አንዱ ግብ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር መሆኑን አስታውሰው ተቋሙ ግቡን ለማሳካት ይበልጥ መሥራት እንዳለበት ነው አጽንኦት የሰጡት።

የቋሚ ኮሚቴው አባል ጋሻው ዳኛው በበኩላቸው ተቋሙ የይዘት ሥራዎች ላይ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚባው ጠቅሰው አቅሙ የተገነባ የሰው ኃይል ወሳኝ በመሆኑ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።

መረጃን በፍጥነትና በጥራት ማቅረብ ተወዳዳሪ ለመሆን ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ኮርፖሬሽኑ በትኩረት ሊሰራበት የሚገባው ሌላው ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።

ኮርፖሬሽኑ ቴክኖሎጂን በስፋት መጠቀም ይገባዋል ያሉት ደግሞ ሌላው የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ መስፍን እርካቤ ናቸው።

ተቋሙ አገራዊ ተልዕኮዎችን ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲያከናውን ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍሰሃ ይታገሱ በበኩላቸው፤ ተቋሙ በአሁኑ ወቅት በ8 የአገር ውስጥ እና በ3 የውጭ ቋንቋዎች መረጃዎችን እያሰራጨ መሆኑን ገልጸዋል።

ተጨማሪ ቋንቋዎችን በመጠቀም ሥርጭት ለማካሄድ ተቋሙ እቅድ የያዘ ቢሆንም ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ በመሆኑ በተጨማሪ ቋንቋዎች ሥርጭት ለመጀመር መቸገሩን ጠቁመዋል።

ቴክኖሎጂ በስፋት ለመጠቀምና ተደራሽነቱን ለማሳደግ ተቋሙ የሚያስፈልገው በጀት በመንግሥት በኩል እንዲቀርብም ጠይቀዋል።

ኮርፖሬሽኑ የይዘት ሥራዎችን የሚያሳድጉ አሰራሮችን እየዘረጋ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው የሰው ኃይሉን ለማብቃትም ቀጣይነት ያለው ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑም አብራርተዋል።

"ሥራዎችን በተሻለ መልኩ ለመከወን የሚረዱ አዋጅና መመሪያ በማዘጋጀት ላይ ነን፤ በዚህ በኩል ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን" ሲሉም አክለዋል።

ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባ ሸጎሌ እያስገነባ ያለው ማስፋፊያ ፕሮጀክት 95 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን ግንባታው ከጀመረ አንድ ዓመት እንደሆነው ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም