መንግስት የፈቀደልን የቤት ኪራይ ክፍያ ይከበርልን-----የሐረር መምህራን ትምህርት ኮሌጅ መምህራን

67
ሀረር መስከረም 24/2011 መንግስት የፈቀደልን የቤት ኪራይ ክፍያ እንዲከበርልን በተደጋጋሚ ላቀረብነው ጥያቄ ምላሽ ተነፍጎናል ሲሉ የሐረር መምህራን ትምህርት ኮሌጅ መምህራን ቅሬታቸውን ገለፁ። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት መምህራን ኮሌጁ ለመምህራን መኖሪያነት ያስገነባቸው ቤቶች ለሌላ አካል መሰጠታቸው አግባብ አለመሆኑንም ተናግረዋል ። መምህራኑ እንዳሉት መንግስት በ2007 ዓ.ም ለመምህራን የፈቀደውና በክልሉ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ የሆነው የቤት ኪራይ ክፍያ እስካሁን ሊከበርላቸው አልቻለም ። “ክፍያው እንዲከበርልን ለኮሌጁና ለሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ ላቀረብነው ጥያቄ ምላሽ ተነፍገናል “ ያሉት መምህራኑ መንግስት ቅሬታቸውን ሰምቶ መፍትሄ እንዲፈልግላቸው ጠይቀዋል። “ኮሌጁ ለመምህራን መኖሪያ የገነባቸው 16 ቤቶችም ለሌላ አካል ተላልፈው መሰጠታቸው አግባብ አለመሆኑን በተደጋጋሚ ቅሬታችንን ብንገልፅም ጥያቄያችንን ተቀብሎ ተግባራዊ የሚያደርግ አካል አጥተናል” ሲሉ መምህራኑ ገልጸዋል። ”በተገነቡ ቤቶቹ  ከ1989 እስከ 1994 አ.ም ኖሪያለሁ” ያሉት የኮሌጁ የትምህርት እቅድና አስተዳደር መምህር አቶ አበበ ወልደሩፋኤል በ1995 ዓ.ም ለእድሳት በሚል ቤቱን እንዲለቁ ተደርጎ ለሌሎች ለማይመለከታቸው አካላት ተላልፎ መሰጠቱን ተናግረዋል ። “ከመምህርነት ጋር ግንኙነት የሌላቸውና በህንጻው ውስጥ የሚኖሩ አካላት የግል መኖሪያ ቤታቸውን አከራይተው ኮሌጁ በሰራቸው ቤቶች ውስጥ መኖራቸው አግባብ ባለመሆኑ የሚመለከተው አካል መፍትሄ ሊፈልግ ይገባል “ ሲሉ መምህሩ ጠይቀዋል ። የኮሌጁ የባይሎጂ መምህር አብዲ ሀሰን “መንግስት የመምህራንን የኑሮ ደረጃ ለመቀየርና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ  ጥረት እያደረገ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት በኮሌጁ መምህራን ላይ በጥቅማጥቅምና መብት ላይ የሚደረገው ተጽዕኖ አግባብነት የሌለው  ነው” ብለዋል ። የኮሌጁ የቋንቋ መምህርት መሰረት  አማረ “በሀገሪቱ የሚገኙ የመንግስት ኮሌጆች ካለፉት ስምንት ዓመታት ጀምሮ ከሚከፈላቸው የስራ ክፍያ ደምወዝ በተጨማሪ አስፈላጊው ጥቅማጥቅምችና የቤት ክራይ ክፍያ እየተሰጣቸው በመሆኑ የኮሌጁ መምህራን  መብታችን ሊከበር ይገባል”ብለዋል ። የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አፈንዲ አብዱልዋሲ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት መላሽ ለመምህራን የተፈቀደው የቤት ኪራይ ክፍያ ተግባራዊ ሳይሆን የቆየው የሌሎች ኮሌጆችን ተሞክሮ ለመቀመር በማስፈለጉ መሆኑን ተናግረዋል ። በተለያዩ ጊዜያት የሌሎች ኮሌጆች ተሞክሮ ተጠንቶ ቢቀርብም በካቢኔው ተቀባይነት ሳያገኝ በመቅረቱ ጊዜ መፍጀቱን አመልክተው ጥያቄውን ለመመለስ  የቀረበው አማራጭ ውሳኔ  እየተጠባበቀ መሆኑንም አቶ አፈዲ  ገልጸዋል። “ መምህራኑ ያነሱት ጥያቄ ለመመለስ በአሁኑ ወቅት የቀረበው አማራጭ ውሳኔ ተሰጥቶበት የካቢኔ ፊርማ ብቻ የቀረው በመሆኑ በተያዘው ሳምንት መጨረሻ ድረስ መፍትሄ ያገኛል” ብለዋል ። ለኮሌጁ ለመምህራን ተብሎ የተገነባው ህንጻ ውስጥ እየኖሩ ያሉት የኮሌጁ የቀድሞ አመራር አካላት መሆናቸውን ብቻ እንደሚያውቁ የገለፁት ኃላፊው የማይመለከተው ሰው ካለ ጉዳዩ ተጣርቶ መፍትሄ እንደሚሰጥበት ተናግረዋል። የኮሌጁ ዲን አቶ አርሰላል አብዲ መምህራኑን ያነሱትን የመኖርያ ቤት ጥያቄ አግባብነት ያለው በመሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሄ የሚሰጠው መሆኑን አስታውቀዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም