የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በቴክኖሎጂው ዘርፍ በጋራ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ከተቋማት ጋር ተፈራረመ

330

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 19/2015/ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ እና "ጂዲሲ ኢትዮጵያ" ከተሰኘ ድርጅት ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢኒጂነር ወርቁ ጋቸና፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወንድማገኘሁ ነገራ እና "ጂዲሲ ኢትዮጵያ" ዋና ስራ አስኪያጅ ኖየል ዳንኤል ተፈራርመዋል።


የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢኒጂነር ወርቁ ጋቸና ስምምነቱ ተቋማቱ በቴክኖሎጂ ዘርፍ በትብብር እንዲሰሩ ያስችላል ብለዋል፡፡


በዚህም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የአገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፍ ለማድረግ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ በትብብር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የምርት ገበያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወንድማገኘሁ ነገራ በበኩላቸው ምርት ገበያው የኦን ላይን ግብይትን ተግባራዊ ለማድረግ እያከናወነ ላለው ተግባር ስምምነቱ እንደሚያግዘው ተናግረዋል።


ስምምነቱ የምርት ገበያ ደንበኞች ባሉበት ሆነው በኢንተርኔት አማካኝነት እንዲገበያዩ ያስችላል ብለዋል።


ስምምነቱ ዓለም አቀፍ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ለመስራት እንደሚያግዝ የተናገሩት ደግሞ የጂዲሲ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ ኖየል ዳንኤል ናቸው።


የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ቀደም ሲል ከፋይናንስ፣ መገናኛ ብዙሀን፣ የግልና መንግስታዊ ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም በጋራ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም