በጋሞ ዞን የተገነባው የጋሞ ባይራ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑ ተገለጸ

189

አርባ ምንጭ፣ ጥር 18 ቀን 2015 (ኢዜአ) በጋሞ ዞን የተገነባው የጋሞ ባይራ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

በዞኑ በአርባ ምንጭ ከተማ በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ተገንብተው ለአገልግሎት ዝግጁ የሆኑት የጋሞ ዞን ባህል ማዕከልና የጋሞ ባይራ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፕሮጀክቶች በክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና አካባቢው ነዋሪዎች ተጎብኝተዋል።

ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉም ተጠቁሟል።

በጉብኝቱ ላይ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘዉዴ የጋሞ ባይራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታው መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ በ16 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን ባለፉት ስምንት ወራት ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ እንዲሆን መደረጉን አብራርተዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ የመማሪያ፣ የማደሪያ፣ የቤተ መጻህትና የቤተሙከራ ክፍሎች እንዲሁም ተማሪዎች የተለያዩ ሙያዎችን የሚቀስሙበት ዎርክሾፖችና ሌሎች መዝናኛ ስፍራዎች ያካተተ ሆኖ መገንባቱን ገልጸዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ በዕዉቀትና በክህሎት የበቁና ተጽዕኖ ፈጣሪ ዜጎችን ለማፍራት ታቅዶ የተገነባ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ በአሁኑ ሰዓት ከዞኑ 14 ወረዳዎችና 6 የከተማ አስተዳደሮች በትምህርታቸዉ ግንባር ቀደም የሆኑ 214 የ9ኛ ክፍል ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር መጀመሩን አመላክተዋል፡፡

በተመሳሳይ የጋሞ ዞን ባህል አዳራሽ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ባለፉት 10 ዓመታት ሲገነባ ቆይቶ በአሁኑ ሰዓት ግንባታዉ ተጠናቆ የዉስጥ ቁሳቁሶችን የማሟላት ስራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አዳራሹ በዉስጡ ከ1 ሺህ 500 እከከ 200 ሰዎችን መያዝ የሚችሉና ዓለም አቀፍ ደረጃቸዉን የጠበቁ 10 የስብሰባ አዳራሾች የያዘ መሆኑ ተመላክቷል።

ለሆቴል፣ ባህል ምርምር፣ ቴአትርና ለስፖርት አገልግሎት የሚዉሉ ክፍሎች የያዘ ዘመናዊ አዳራሽ መሆኑንም አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል፡፡

በመንግስትና በህዝብ ተሳትፎ በ1 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ካፒታል የተገነቡት እነዚህ ፕሮጀክቶች በቅርቡ ተመርቀዉ ሙሉ በሙሉ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በጉብኝቱ በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና ከጋሞ ዞን ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተዉጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም