በኢትዮጵያ የጊኒ ዎርም በሽታን ከዓለም ለማጥፋት የተቀመጠውን ግብ ቀድሞ ለማሳካት እየተሰራ ነው

ጋምቤላ ፤ ጥር 18 ቀን 2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የጊኒ ዎርም በሽታን እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2030 ከዓለም ለማጥፋት የተቀመጠውን ግብ ቀድሞ ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ለሁለት ቀናት በጋምቤላ ከተማ ሲካሄድ የቆየው 27ኛው የጊኒ ዎርም ማጥፋት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ ተጠናቋል።

በዚህ ወቅት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ፤ የጊኒ ዎርም በሽታን ከጋምቤላ ብሎም ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ኢንስቲትዩቱ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በጋምቤላ ክልልና በደቡብ ኦሞ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የበሽታው ስርጭት ይታይ የነበረው አሁን ላይ በጋምቤላ ክልል ሁለት ወረዳዎች ብቻ የበሽታው ስርጭት በተወሰነ ደረጃ መኖሩን ጠቅሰዋል።

እንዲሁም በሽታውን የማጥፋት ስራ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1993 ሲጀመር በዓመት በበሽታው ይጠቁ የነበሩት ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 250 አካባቢ የነበረው በተጠናቀቀው የአውሮፓዊያን ዓመት በአንድ ሰው ላይ ብቻ መገኘቱን አስረድተዋል።

እንደ ኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ገለፃ ፤የበሽታው የመግደል ምጣኔ ዝቅተኛ ቢሆንም በሰዎች ላይ የሚያደርሰው የማህበራዊና የስነ-ልቦናዊ ጫና ከፍተኛ ነው።

ኢንስቲትዩቱ ከጤና ሚኒስቴርና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የጀመራቸውን የተቀናጀ የምርምር ስራን በማጠናከር እስከ ቀጣይ ዓመት በሰው ላይ ያለውን የስርጭት መጠን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ትኩረት የሚሹ በሽታዎች አስተባባሪ ዶክተር ዘየደ ከበደ በበኩላቸው፤ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1980ቹ በዓለም 21 ሀገራት 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህዝብ ገደማ በጊኒ ዎርም በሽታ ይጠቃ እንደነበር አስታውሰዋል።

ሆኖም ሀገራት የሽታውን ስርጭት ለማጥፋት ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት አሁን ወደ መጥፋት መቃረቡን ገልጸዋል።

ለዚህም በማሳያነት የጠቀሱት በተጠናቀቀው የአውሮፓዊያን ዐመት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአምስት የአፍሪካ ሀገራት 13 ሰዎች ብቻ በበሽታው ተጠቅተው መገኘታቸው ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት የጊኒ ዎርም በሽታን እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2030 ከዓለም ለማጥፋት ግብ ጥሎ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ ያለው የጊኒ ዎርም ስርጭት ቀደም ሲል ከነበረው በእጅጉ መቀነሱን የገለጹት አስተባባሪው ፤ በኢትዮጵያ አሁን እየተከናወኑ ያሉት ስራዎች ተጠናክረው ከቀጠሉ ጊኒ ዎርም ለማጥፋት ከተቀመጠው ግብ ቀድማ መሳካት እንደሚቻል ተናግረዋል።

በካርተር ማዕከል የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶክተር ዘሪሁን ታደሰ እንዳሉት፤ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2022 ኢትዮጵያ የጊኒ ዎርም በሽታ የማጥፋት እቅድ አፈፃፀም ከምንጊዜውም በላይ የተሻለ ነበር።

በተከናወነው መልካም አፈፃፀም ምክንያትም በዓመቱ በአንድ ሰው፣ በሁለት ዝንጀሮዎችና በአንድ ውሻ ላይ ብቻ የበሽታው ስርጭት መታየቱን ጠቁመዋል።

የጊኒ ዎርም የማጥፋት ዘመቻ ረዘም ያለ ጊዜ የፈጀ ቢሆንም አሁን ላይ ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ ነው ያሉት ደግሞ የጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሩት ጋትዊች ናቸው።

ከሶስት ዓመታት በፊት በየዓመቱ ከ10 በላይ ሰዎች በበሽታው ይጠቁ የነበረው አሁን ላይ አንድ ሰው ላይ ብቻ መከሰቱን ጠቁመው ፤ ይህም የሚያሳየው በዘረፉ ውጤታማ ስራ መሰራቱን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም