የከተማዋ ነዋሪዎች ፍሳሽን በአግባቡ ሊያስወግዱ ይገባል

ጥር 18/2015 /ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ፍሳሽን በአግባቡ እንዲያስወግዱ የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ጥሪ አቀረበ።

በአዲስ አበባ ከተማ ከተለያዩ ቢሮዎች የተውጣጡ የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የቃሊቲና የቦሌ ቡልቡላ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎችን፣ የለገዳዲ ግድብን እንዲሁም የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የሥልጠና ልህቀት ማዕከልን ጎብኝተዋል።

የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ኬዝ ማናጀር ሚስባህ ኤልያስ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ጣቢያው ፍሳሾች የሚጣሩበት በዋናነት የሕብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅና የአካባቢን ስነ-ምህዳር ለመንከባከብ የሚያገለግል ነው።

የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ለመስኖ አገልግሎት የሚውል ውኃ፣ ለባዮ ጋዝ አገልግሎት የሚውል ፍሳሽና ለኮምፖስትነት የሚውሉ ተረፈ-ምርቶች በማውጣት ላይ ትኩረት ማድረጉን ነው ያስረዱት።

በተለይም በማጣራት ሂደቱ የሚገኙ ተረፈ-ምርቶቹን ለታሰበላቸው ዓላማ በማዋል ለሕብረተሰቡ ጠቀሜታ እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ማጣሪያ ጣቢያው አሁን ላይ ከሰባት ክፍለ ከተሞች በመስመርና በተሸከርካሪ ፍሳሽ እየተቀበለ በማጣራት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

የጣቢያው የፍሳሽ ማጣራት አቅም በቀን 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ መሆኑን ገልጸው፤ አሁን ላይ ግን 70 ሺህ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ ብቻ እያጣራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም የነዋሪዎች የፍሳሽ መስመር ዝርጋታ ላይ ውስንነት መኖሩን ጠቁመው፤ ለዚህም ከቤት ለሚወጡ መስመሮች ተጨማሪ ቅጥያዎች መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም