በምስራቅ ሸዋ ዞን በሜካናይዜሽን የታገዘ ከ203 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ ስንዴ ተሸፍኗል

168

አዳማ ጥር 17/2015 /ኢዜአ/ በምስራቅ ሸዋ ዞን በሜካናይዜሽን በመታገዝ ከ203ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ መሸፈኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 200ሺህ ሄክታር ለማልማት ታቅዶ በአስከ አሁኑ ስራ ከ203ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈን መቻላቸውን ገልጸዋል።

ከእቅድ በላይ ማሳካት የተቻለውም ካለፉት ዓመታት ልምድ ተነስተው በተሰራው ስራ ነው ያሉት አቶ መስፍን፤ በዚህም ቀደም ተብሎ ከጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ የአዝዕርት ስራ በመጀመራቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ለአርሶ አደሩ ተገቢውን ስልጠና ከመስጠት በተጨማሪ እንደ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር የመሳሰሉ ግብዓቶችን በጊዜው ማሟላታቸው ስራውን እንዳፋጠነላቸው ተናግረዋል።

በዚህም ከ400ሺህ ኩንታል በላይ የአፋር ማዳበሪያና 300ሺህ ኩንታል የስንዴ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መቅረቡን ጠቅሰዋል።

በዞኑ የበጋ ስንዴ መስኖ ልማቱ ሙሉ በሙሉ በሜካናይዜሽንና የተለያዩ የቴክኖሎጂ ግብዓት በመጠቀም እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ አስፈላጊዎቹን ማሽነሪዎች በማቅረብ ላይ ዞኑ ትኩረት ሰጥቶበት ከሰራቸው ስራዎች መሆኑን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ በተፈጥሮ ዝናብ ብቻ ተወስኖ በዓመት አንድ ጊዜ ሲያመርት የነበረውን በዓመት ሶስቴ እንዲያመርት ከማስቻል ባለፈ የአርሶ አደሩ የስራ ባህል እንዲቀየር በማድረግ ዓመቱን ሙሉ በልማት ስራ እንዲያሳልፍ አድርጓል ብለዋል።

ለዘንድሮው የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት በናፍጣ የሚሰሩ 1ሺህ 800 የውሃ መሳቢያ ሞቶሮች መቅረባቸውን ጠቅሰው በዞኑ ባጠቃላይ ከ13ሺህ በላይ የውሃ መሳቢያ ሞቶሮች በመስኖ ስንዴው ልማት ላይ መዋላቸውን ገልጸዋል።

ያለፈው ዓመት በዞኑ 65ሺህ ሄክታር በመዝራት 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል መገኘቱን የገለጹት ሃላፊው በዘንድሮ ዓመት በበጋ ስንዴው ከተሸፈነው መሬት ላይ 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ለማግኘት እንዳቀዱም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ቀደም ብሎ የተዘራው ስንዴ ምርት እየደረሰ መሆኑን የገለጹት አቶ መስፍን ምርቱን በሜካናይዜሽን ብቻ ለመሰብሰብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

ከስንዴ ልማቱ ጎን ለጎን ዞኑ የሸንኮራ አገዳ፣ ቲማትም፣ ሽንኩርት የመሳሰሉ አትክልቶችም በስፋት እያለማ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እየሆነ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም