የቅመማ ቅመም ምርትን በብዛትና ጥራት የማምረት ስራ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል- የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ

286

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 17/2015 የቅመማ ቅመም ምርትን በብዛትና ጥራት የማምረት ስራ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ሥርዓት አፈጻጸም በተመለከተ ግምገማ አካሂዷል።

የ2013/14 ዓ.ም የተከናወነ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት መነሻ በማድረግ በተደረገው ውይይት በተለይም የቅመማ ቅመም ምርትን በተመለከተ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑ ተመልክቷል።

በመሆኑም የዘርፉን ልማት ለማስፋፋት ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑ ተጠቁሞ የምርጥ ዘር አቅርቦት፣ ቴክኖሎጂ፣ የበሽታ ቁጥጥርና ምርት አሰባሰብ ላይ ያሉ ክፍተቶች ሊስተካከሉ ይገባልም ነው የተባለው።

የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት፣ አርሶ አደሮችን መደገፍና የምርት ጥራት ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ተብሏል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ፤ የቅመማ ቅመም ምርትን ለማሳደግ የሚረዱ ምርጥ ዘሮችን ከተለያዩ የምርምር ማዕከላት ጋር በመሆን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተያዘው ዓመት በኦሮሚያ ክልል ኢሉ አባቦራ ዞን ለ6 ሺህ አርሶ አደሮች የኮሮሪማ ዝርያ እንደተሰራጨም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት።

ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ 16 የቅመማ ቅመም ዓይነቶች መለየታቸውን ጠቁመው የምርቶቹን ጥራት ማስጠበቅ ላይ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ጎንደር የበርበሬ ምርት እንዲሁም በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን በሮዝመሪ ምርት የተሻለ ተሞክሮ መኖሩን ጠቁመው ተሞክሮው ወደ ሌሎች ክልሎች እንዲሰፋ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።

የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታ ሶፊያ ከሳ፤ ኢትዮጵያ በቅመማ ቅመም ምርት ልማት ያላትን እምቅ ኃብት ለመጠቀም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የቅመማ ቅመም ግብይትና ጥራት ቁጥጥር መመሪያ መዘጋጀቱን ጠቅሰው በባለሙያዎችና በባለድርሻ አካላት ተገምግሞ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ፤ በቅመማ ቅመም ልማት ዘርፉ በሽታን መከላከል፣ የምርት ጥራትን ማስጠበቅና የተሻለ አሰራርና አመራረትን መከተል ይገባል ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ አሬሬ ሞሲሳ፤ አገሪቷ ከዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ አልተጠቀመችም፤ ባለስልጣኑ ሊሰራበት ይገባልም ነው ያሉት።

በቡና ምርት እየተገኘ ያለውን የውጭ ምንዛሬ በቅመማ ቅመም ዘርፍም ማስቀጠል ተገቢ መሆኑን አመላክተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው የቅመማ ቅመም ምርት ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን ከባለሥልጣኑ ጋር በተሰናሰነ መንገድ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም