በድሬዳዋ የነዋሪዎችን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ከንቲባ ከድር ጁሃር

152

ድሬዳዋ፤ ጥር 17 ቀን 2015(ኢዜአ) በድሬዳዋ አስተዳደር የገጠርና የከተማ ነዋሪዎች የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአስተዳደሩ ከንቲባ ከዲር ጁሃር አስታወቁ።

ከንቲባው በድሬደዋ ዋሂል የገጠር ቀበሌ በ14 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ህንፃ በመረቁበት ወቅት፤ የነዋሪዎችን በተለይም የወጣቱን የስራ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተለይ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የገጠር ነዋሪዎችን የመንገድ፣የጤና የንፁህ መጠጥና የመስኖ ውሃ ችግሮችን ለማቃለል የተከናወኑ ፕሮጀክቶች መሠረታዊ ለውጥ እያመጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

"ዛሬ መርቀን ለአገልግሎት ዝግጁ ያደረግነው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዓመታት የገጠር ነዋሪዎች ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት አስተዳደሩ ያለውን ቁርጠኝነት ማሳያ ይሆናል " ብለዋል።

ትምህርት ቤቱ የሚጠበቅበትን አገልግሎት እንዲሰጥ ለመማር ማስተማር የሚያገለግሉ ቁሶች ከትምህርት ቢሮ ጋር በመሆን በአጭር ጊዜ የማሟላት ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል ።

በቀጣይም የከተማውን ሆነ የገጠሩን ነዋሪ ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

በዋሂል ገጠር ክላስተር ስር የሚገኙት ቀበሌዎች አመራሮችና በየደረጃው የሚገኘው ነዋሪ ትምህርት ቤቱን በጥንቃቄ በመንከባከብ ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉካ መሐመድ ፤ 14 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የወጣበት ትምህርት ቤት በ6 የገጠር ቀበሌዎች የሚገኙ 1ሺህ 600 ተማሪዎች በሁለት ፈረቃ ይማሩበታል ብለዋል።

ትምህርት ቤቱ 16 የመማሪያ ክፍሎችን ጨምሮ ለመማር ማስተማሩ የሚያስፈልጉ ሌሎችም መገልገያዎችን ማካተቱን ጠቁመዋል ።

በትምህርት ቤት ግንባታ ላይ የአካባቢው ነዋሪዎች በገንዘብ ፣በጉልበትና መሬትን በማዘጋጀት ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ያሉት ወይዘሮ ሙሉካ፤ በግንባታው ሂደት ከ100 በላይ ወጣቶች የስራ ዕድል ተጠቃሚ በመሆን የስራ ልምድ ቀስመዋል ብለዋል።

በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር የካቢኔ አባላትና የብልጽግና ጽህፈት ቤት አመራሮች እንዲሁም ነዋሪዎች መገኘታቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም