ምክር ቤቱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የፋይናንስ አሰራር ሥርዓትን የጣሰ ክፍያን እንዲያቆም አሳሰበ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 17/2015 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን እየፈጸመ ያለውን የፋይናንስ አሰራር ሥርዓትን የጣሰ ክፍያ እንዲያቆም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2013 በጀት ዓመት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣንን የኦዲት ሪፖርት አድምጧል። 

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ ባቀረቡት ሪፖርት ባለሥልጣኑ በተጠቀሰው በጀት ዓመት ኦዲት ግኝት ላይ በቂ የሰነድ ማስረጃ ባለመስጠቱ አስተያየት ሊሰጥበት አልተቻለም ብለዋል። 

በ2013 ዓ. ም. በተደረገ የኦዲት ግኝት በገቢ ሂሳብ ላይ 10 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር እንዲሁም በወጪ ሂሳብ 19 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር የማስረጃ ሰነድ አለማቅረቡን አስታውሰዋል።

አሁን ላይ የማስተካከያ ኦዲት ሲደረግ ወደ 6 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ጉድለት ላይ የሰነድ ማስረጃ እንዳልቀረበ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የደመወዝና የጥቅማጥቅም ጉዳዮችን መወሰን የሚችለው የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሆኖ ሳለ ከተቋሙ እውቅና ውጭ የትራንስፖርት አበል በሚል ለሠራተኞች ክፍያ እየፈጸመ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በዚህም የጸደቀ ደምብ በሌለበት ሁኔታ የትራንስፖርት አበል በሚል ከሐምሌ 1 ቀን 2012 እስከ ሰኔ 2013 ዓ. ም. ከ153 ሺህ ብር በላይ አላግባብ ወጪ አድርጓል። 

ይህም በሚመለከተው አካል ፈቃድ ሳያገኝ ክፍያ መፈጸሙን የኦዲተር ሪፖርት እንዳመላከተና፤ ተቋሙ ማስተካከያ እንዲያደርግ ቢጠየቅም አሁንም ክፍያ መፈጸም መቀጠሉን አስረድተዋል። 

በተጨማሪም ባለሥልጣኑ በዋና ኦዲተር ከተረጋገጠበት አሥር የሪፖርት ግኝት ውስጥ በአምስቱ ላይ ብቻ ማስተካከያ ማድረጉ በሪፖርት ተመላክቷል። 

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጂማ ዲልቦ በበኩላቸው፤ ችግሩ የተፈጠረው በባለሥልጣኑ የፋይናንስ ኃላፊ የገንዘብ ሚኒስቴር 'የኢፍሚስ' ሲስተም አጠቃቀም ጉድለት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። 

በመሆኑም ይህንን ችግር የፈጠረው የፋይናንስ ኃላፊ ከቦታው እንዲነሳ መደረጉን ገልጸው፤ አሁን ላይ የኦዲት ግኝቱን ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ከዚህም በተጨማሪ ገንዘብ ሚኒስቴር በ'ኢፍሚስ' አጠቃቀም ላይ ተጨማሪ ሥልጠና ለሠራተኞቻቸው እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል። 

ሰነዶች በአንድ ኮፒ ብቻ በመቀመጣቸው ለኦዲተር እንዳልቀረቡና በተቋማቸው የሰነድ አያያዝ ችግር መኖሩን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል። 

ዳይሬክተሩ ችግሩ እንዳለ ተቀብለው የኦዲት ግኝቱን ለማስተካከል ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በጋራ ለመፍታት እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው፤ ባለሥልጣኑ ከሕግና አሰራር ውጭ ለሠራተኞቹ ደምብ በመጣስ ክፍያ መፈጸም እንደሌለበትና ክፍያ መፈጸም የሚችለው በሚመለከተው አካል ሲጸድቅ ብቻ በመሆኑ ይህ ሊስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል። 

ባለሥልጣኑ የኦዲት ግኝቱን በተመለከተ እስከ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም የተስተካከለውን የኦዲት ማሻሻያ ሪፖርት ማቅረብ እንዳለበት ገልጸዋል። 

የኦዲት ማሻሻያ አፈጻጸም ሪፖርት የኦዲት ግኝቱ ሙሉ በሙሉ እስኪስተካከል ድረስ በየሦስት ወሩ እንዲያቀርብ አሳስበዋል። 

ያላግባብ የተከፈለ ገንዘብ ተመላሽ እንዲሆንና መመሪያን በጣሱ ሠራተኞችና አመራሮች ላይ ተገቢውን አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ በአንድ ወር ውስጥ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲያቀርብ አሳስበዋል። 

የገንዘብ ሚኒስቴርና የፍትሕ ሚኒስቴር በየፊናቸው መመሪያውን በጣሱና ሕግን በማያከብሩ የሥራ ኃላፊዎች ላይ በሥልጣን እርከኑ መወሰድ ያለበትን አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ በአንድ ወር ውስጥ እንዲያሳውቅ አሳስበዋል።  

የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ በበኩላቸው፤ የመረጃ አያያዝ ክፍተትን ለማስተካከልና የ'ኢፍሚስ' አጠቃቀም ላይ ሥልጠና እንዲሰጥ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር እንሰራለን ብለዋል። 

ባለሥልጣኑ ኃላፊውን ከቦታው ማንሳቱ ጥሩ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ የተቋሙን አሰራር በተጠናከረ መልኩ እንደሚከታተሉ አሳስበዋል። 

የኦዲት ግኝቱ ሙሉ ለሙሉ እንዲስተካከል ድጋፍና ክትትል እናደርጋለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም