በየካቲት ወር ለሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ እየተደረጉ ያሉ የዝግጅት ስራዎች ግምገማ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በየካቲት ወር ለሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ እየተደረጉ ያሉ የዝግጅት ስራዎች ግምገማ ተካሄደ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 17/2015 በመዲናዋ በየካቲት ወር ለሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ እየተደረጉ ያሉ የዝግጅት ስራዎች ግምገማ ተካሄደ።
36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እና 42ኛው የህብረቱ አስፈፃሚዎች ጉባኤ እ.አ.አ ከየካቲት 15 እስከ 19 በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ሰላሳ ተቋማትን በአባልነት የያዘ ብሄራዊ የዝግጅት ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
ብሄራዊ ኮሚቴው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት የእስካሁን የዝግጅት ስራዎችን ገምግሟል።
በግምገማው ላይ እንደተገለፀው ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎች በባለድርሻ ተቋማት እየተከናወኑ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህ ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉባኤው ኢትዮጵያ ከነበረችበት ፈታኝ ሁኔታ እየወጣች ባለችበት ወቅት የሚካሄድ እንደመሆኑ አዎንታዊ ገፅታ ለመገንባት እድል ይፈጥራል ብለዋል።
የህብረቱን ጉባኤ አምና ውጤታማ በሆነ መልኩ ማካሄድ መቻሉን ያስታወሱት አቶ ደመቀ የነበሩ ጉድለቶችን በማሻሻል በተሻለ ስኬት ዘንድሮ ማስተናገድ እንደሚገባ አስታውቀዋል።
ለስኬቱም ባለድርሻ ተቋማት በተናበበ መልኩ ቅንጅትን በመፍጠር እንዲሰሩ አሳስበዋል።
የብሄራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ አምና የነበረውን አፈፃፀም በመገምገም ወደ ስራ መገባቱን ገልፀዋል።

የጉባኤው ተሳታፊ እንግዶች የሚኖራቸው ቆይታ የተሳካ እንዲሆን ከወዲሁ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በእቅድ መሰረት እየተከናወኑ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የጉባኤው መካሄድ ለሃገራችን ገፅታ ግምባታ እና በኢኮኖሚ ረገድ ከፍ ያለ ጥቅም ሊያስገኝ በሚችል ደረጃ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።
የዝግጅት ግምገማው የብሄራዊ ኮሚቴው አባል ተቋማት በቀሪ ጊዜያት ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩባቸውን አቅጣጫዎች በማስቀመጥ መጠናቀቁን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።