የተፋሰስ ልማት የቤተሰብ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን በመቀነስ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - የድሬዳዋ አስተዳደር

289

ድሬዳዋ (ኢዜአ) ጥር 17/2015 የተፋሰስ ልማት ስራ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት ከማገዝ ባለፈ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን በመቀነስ አይነተኛ ሚና እያበረከተ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር አስታወቀ።

የዘንድሮ የበጋ ወቅት የተፋሰስ ልማት ስራ በድሬዳዋ በ38ቱ ገጠር ቀበሌዎች ዛሬ ተጀምሯል።

በአስተዳደሩ "የተፋሰስ ልማት ለሌማት ትሩፋት" በሚል መሪ ሃሳብ ለሶስት ሳምንት የሚካሄደውን የተፋሰስ ልማት ስራ ያስጀመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ናቸው።

ከንቲባ ከድር ጁሃር በወቅቱ እንዳሉት ከተጎራባች አካባቢዎች ጋር በተቀናጀ መንገድ በመተግበር ላይ የሚገኘው የተፋሰስ ልማት ምርትና ምርታማነት በመጨመር የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ አይነተኛ ሚና እያበረከተ ነው።

"ባለፉት አመታት የተሰሩ ልማቶች ተጨባጭ ውጤት አስገኝተዋል" ብለዋል።

"በተለይ የአፈርና የውሃ ጥበቃና እንክብካቤ ተግባራት ምርትና ምርታማነት በማሳደግ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ስራዎችን ፍሬያማ አድርገዋል" ሲሉ አክለዋል።

በተለይ በድሬዳዋ ልማትና ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በአመታት ልዩነት ሲፈጥር የነበረውን የጎርፍ ችግር በማቃለል በኩል የተፋሰስ ልማቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ከንቲባው አመልክተዋል።

የተፋሰሱ ልማት በአስተዳደሩ ከተጀመረው የሌማት ትሩፋት መረሃ-ግብር ጋር በማቆራኘት በገጠር በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጡን ተግባራት ስኬታማ ለማድረግ አመራሩ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በተለይ በተጀመረው የተፋሰስ ልማት ከአፈርና ውሃ ጥበቃ ባሻገር የትምህርት፣ የጤና እንዲሁም ማህበረሰብ አቀፍ የጤና አገልግሎት ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ በትኩረት እንደሚሰራ ከንቲባው አስታውቀዋል።

የድሬደዋ አስተዳደር የግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ በበኩላቸው "ባለፉት ስምንት አመታት የተከናወኑት የተፋሰስ ልማቶች አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ተግባርን ስኬታማ እያደረጉ ናቸው" ብለዋል።

በአስተዳደሩ ባለፉት ስምንት አመታት በ31ሺህ 840 ሄክታር የተራቆተ መሬት ላይ በተከናወነ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራዎች የመሬት መራቆትን በ33 በመቶ በመከላከል 229ሺ ቶን አፈር በጎርፍ ከመታጠብ መከላከል መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የተፋሰስ ልማት ስራው በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ዕውን እንዲሆንና በእንሰሳት፣ በዶሮ፣ በንብ ማነብና በማር ምርቶች፣ በመኖና በደን ልማት የላቀ ውጤት ለማምጣት ወሳኝ አበርክቶ እንደሚኖረው አመላክተዋል።

በተፋሰስ ልማቱ በቀበሌው የደረቁ ምንጮችና ወንዞች በመመለሳቸው የመስኖ ልማት ተጠቃሚነታችንን ማረጋገጥ አስችሏል" ያሉት ደግሞ በአስተዳደሩ የለገኦዳ ጉኑንፈታ ቀበሌ ሊቀ-መንበር አቶ ሙሜ አደም ናቸው።

በርካታ ቤተሰቦች ምርትና ምርታማነታቸውን በማሳደግ የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ መቻላቸውን አውስተው "በዘንድሮው የበጋ ወቅት 225 የተደራጁ ቡድኖች በቀበሌው በተራቆተ 53 ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራዎች ማከናወን ጀምረዋል" ብለዋል።

በተጨማሪም ከ8ሺ በላይ የችግኝ ጉድጓዶች ከመቆፈር በተጨማሪ 645 ሄክታር መሬትን ለእርሻ የማመቻቸት ስራ እንደሚከናወን ገልፀዋል።

ዛሬ በ38 ገጠር ቀበሌዎች የተጀመረውና ለ21 ቀናት በ5ሺህ 550 ሄክታር መሬት ላይ የሚካሄደው የተፋሰስ ልማት ስራ የመሬት መራቆት ችግርን በ3 ነጥብ 7 በመቶ ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከአስተዳደሩ የተገኘው መረጃ አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም