የገንዘብ ሚኒስትሩ በመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ ከተለያዩ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የገንዘብ ሚኒስትሩ በመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ ከተለያዩ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 17/2015 የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የማቋቋም ፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች ጋር መወያየታቸው ተገለጸ፡፡
በውይይቱ ወቅት በመልሶ ማቋቋም ሴክሬቴሪያትና በባለድረሻ አካላት የተጠናውና በግጭት አካባቢዎች የደረሰውን ጉዳት መጠን በየዘርፉ መቅረባቸው ተገልጿል።
በሚቀጥሉት አምስት አመታት የመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክቱ ዝርዝር አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበትም ተመላክቷል፡፡
የመልሶ ማቋቋሙ ፕሮጀክት ዝርዝር አፈጻጸም በቅርቡ ለህዝቡና ለባለድረሻ አካላት ይፋ አንደሚደረግ አቶ አህመድ ሽዴ ገልጸዋል።
በመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክቱ የላቀ ድርሻ ያላቸው የትምህርት፣ የጤና፣ የግብርና፣ የውሃና ኢነርጂ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ በፕሮጀክቱ አፈጻጸም ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸው ሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በርካታ ስራ ስለሚጠብቃቸው የፕሮጀክት አፈጻጸም አቅማቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የትምህርት፣ የጤና፣ የግብርና፣ የውሃና ኢነርጂ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ እና ሌሎች ሚኒስትሮች በየዘርፋቸው በመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክቱ መካተት አለባቸው ያሏቸውን ሀሳቦች በግብአትነት ማቅረባቸው ተመላክቷል።
የገንዘብ ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መረጃ የሴቶችና የህጻናት ጉዳይም ትኩረት አንዲሰጠው መጠየቁን አስታውቋል፡፡