ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ያላትን የሠላም ማሥከበር ተሳትፎ አጠናክራ ትቀጥላለች- ሜጄር ጄኔራል አዳምነህ መንግስቴ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 17/2015 ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ያላትን የሠላም ማሥከበር ተሳትፎ አጠናክራ እንደምትቀጥል የመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል አዳምነህ መንግስቴ ገለጹ፡፡

ሜጄር ጀነራሉ አክለውም ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ያላትን የሰላም ማስከበር ተሳትፎ አሁን ባለው አግባብ ማስቀጠል እንድትችል ውጤታማ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሜጄር ጄኔራል አዳምነህ በማዕከሉ በተካሄደው የ6 ወር የስራ አፈፃፀም ውይይት ላይ ሀገራችን በአለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያላትን ተሳትፎ ለማሥቀጠል የነበሩንን ጠንካራ ጎኖች ማሣደግና ድክመቶችን ማረም ይገባል ብለዋል፡፡

በሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የመንግስት ንብረቶችን በመጠገንና ወደ ስራ በመመለስ የተከናወኑ ወጭ ቆጣቢ አሰራሮች በሌሎችም ክፍሎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ሲሉ አርአያነታቸውን አድንቀዋል፡፡

በውይይቱም ከባለድርሻ አካላት ጋር የነበሩ ውጤታማ ስራዎች እና ስልጠናዎች፣ ለአለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሰራዊትን በብቃት የማዘጋጀት እና የግንባታ ስራዎች በጥንካሬ ተገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የሎጅስቲክስ ዝግጅት ስምሪትና ድጋፎች፣ የዘመቻ ስምሪት እና ሚሽን ክትትል፣ አስተዳደራዊ እና የፋይናንስ ስራዎች፣ የስራ አፈፃፀም ሂደቶች እንዲሁ በጥንካሬ ተጠቅሰዋል፡፡

በአለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የተሰማራው የሰላም አስከባሪ ሃይል የሚያከናውናቸውን ውጤታማ የሰላም ማስከበር ስራዎች በማስቀጠል እና የሀገራችንን ተሠሚነት በተሻለ ደረጃ ማሣደግ እንደሚገባ አዛዡ ገልፀዋል፡፡

ክፍተቶችን ለመሙላት በስልጠና አቅምን በየሙያ ዘርፉ በማሳደግ የአቅም ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸውም ሜጄር ጄኔራል አዳምነህ መንግስቴ ማሳሰባቸውን ከመከላከያ ይፋዊ የማህበራዊ ገጽ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም