ዓለም አቀፉ የህፃናት አድን ድርጅት በጋምቤላ ክልል ያለውን የክትባት አገልግሎቶች ለማጠናከር ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፉ የህፃናት አድን ድርጅት በጋምቤላ ክልል ያለውን የክትባት አገልግሎቶች ለማጠናከር ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ

ጋመቤላ (ኢዜአ) ጥር 16/2015 ዓለም አቀፉ የህፃናት አድን ድርጅት (Save the Children) በጋምቤላ ክልል ያለውን የክትባት አገልግሎቶች ለማጠናከር ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የሞተር ሳይክሎችና የማቀዝቀዣ ፍሪጆች ድጋፍ አደረገ።
ድርጀቱ ድጋፉን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በተገኙበት ለክልሉ ጤና ቢሮ አስረክቧል።

በድርጅቱ የኢትዮጵያ ምክትል ተጠሪ አቶ ሲሳይ ስዩም በርክክቡ ወቅት ድርጅቱ ድጋፉን ያደረገው በክልሉ በሚገኙ 11 ወረዳዎችና ሶስት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ያለውን የክትባት አገልግሎት ለማጠናከር ነው ብለዋል።

በድጋፍ ከተሰጡት ቁሳቁሶች መካከል 44 ሞተር ሳይክሎች እና 38 በጸሃይ ብርሃን የሚሰሩ ማቀዝቀዣዎች መሆናቸውም ተጠቅሷል።
ድርጅቱ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የህፃናት ጤና አገልግሎቱን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው በቀጣይም በዘርፉ የተጀመሩ ድጋፎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ በበኩላቸው የተለገሱት የሞተር ሳይክሎችና በፀሃይ ብርሃን የሚሰሩ ማቀዝቀዣዎች በክልሉ ራቅ ባሉ አካባቢዎች የክትባት አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የጎላ ፋይዳ እንዳላቸው ገልጸዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ለዘርፉ አገልግሎት እንዲውሉ የተለገሱትን ግብዓቶች በአግባቡ በመጠቀም መስራት ከቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ በክልሉ የክትባት ተደራሽነትና ፍትሃዊነትን ማረጋገጥ ይችላል ብለዋል።
ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የክልሉን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ከአጋር ድርጅቶች ጋር የጀመረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዶክተር ደረጀ አስታውቀዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኳዋይ ጆክ በርክክቡ ወቅት ዓለም አቀፉ የህፃናት አድን ድርጅት የክልሉ የህፃናትና ሌሎች የክትባት አገልግሎቶችን ለማጠናከር ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ድርጅቱ በቀጣይ የህፃናት የጤና አገልግሎትን በማሻሻል ጤናማ ትውልድ ለመገንባት ለተቀየሰው ግብ መሳካት የጀመረው ድጋፍ እንዳይለያቸው ጠይቀዋል።
ድጋፎቹ በክልሉ ራቅ ባሉ አካባቢዎች ይታይ የነበረውን የክትባት ተደራሽነት ችግር ለማቃለል እንደሚያግዙ የገለጹት ደግሞ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሩት ጋትዊች ናቸው።
በድጋፍ የቀረቡት ሞተር ሳይክሎችና ፍሪጆች በቅርቡ ለወረዳዎች እንደሚሰራጩና ለታለመላቸው አገልግሎት እንደሚውሉም ተናግረዋል።