በመዲናዋ በወሳኝ ኩነት አገልግሎት ላይ በሕገ-ወጥ ተግባራት ተሳትፈው የተገኙ 57 አመራሮች ተጠያቂ ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ በወሳኝ ኩነት አገልግሎት ላይ በሕገ-ወጥ ተግባራት ተሳትፈው የተገኙ 57 አመራሮች ተጠያቂ ሆኑ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 16/2015 የአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ በሕገ-ወጥ ተግባራት ላይ ተሳትፈው የተገኙ 57 አመራሮችን በሕግና በአስተዳደራዊ እርምጃ ተጠያቂ ማድረጉን አስታወቀ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዮናስ አለማየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በወሳኝ ኩነት አገልግሎት ዙሪያ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛል።
የአገልግሎት አሰጣጡን የተሳለጠና ቀልጣፋ ለማድረግ እንዲሁም በአሰራር ሂደቱ ችግር የሚፈጥሩ አካላት ተጠያቂ እየተደረጉ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ከወሳኝ ኩነት አገልግሎት ጋር በተገናኘ በሕገ-ወጥ ተግባራት ላይ ተሳትፈው የተገኙ 57 አመራሮች በሕጋዊና አስተዳደራዊ አሰራር ተጠያቂ መደረጋቸውን ገልጸዋል።
በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱ በሕገ-ወጥ ተግባር ላይ የተሳተፉ አራት ደላሎችና 32 ተገልጋዮችም በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በሕግ ተጠያቂ የሆኑት ተገልጋዮች በሕገ-ወጥ መንገድና በሐሰተኛ ሰነዶች ለመገልገል የሞከሩ ናቸው።
የነዋሪነት መታወቂያ በማመሳሰል በሕገ-ወጥ መንገድ ማተምን ጨምሮ በዚሁ ሥራ በጥቅም የተሳሰሩ ሙያተኞችንና ደላሎችን በሕግ ተጠያቂ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የወንጀል ድርጊቱ ተሳታፊ ሆነው በተገኙት አመራሮችና ባለሙያዎች ላይ የሕግ ተጠያቂነትን ጨምሮ ከኃላፊነት ማንሳትና ከምደባ ውጭ የተደረጉ መኖራቸውንም አብራርተዋል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አክለውም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 የወሳኝ ኩነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት በሕግ ተጠያቂ መደረጋቸውን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።
በወቅቱ የነበሩት ኃላፊ በሕገ-ወጥ መንገድ ለውጭ አገር ዜጋ የጋብቻ ሰርተፊኬት ሲሰጡ እጅ ከፍንጅ በመያዛቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 የወሳኝ ኩነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት በተመሳሳይ ወንጀል በሕግና አስተዳደር ተጠያቂ ተደርገዋል ነው ያሉት።

የወሳኝ ኩነት አገልግሎት በቅሬታና በመልካም አስተዳደር ችግር ከሚጠቀሱ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአሰራር ማሻሻያው እንዳለ ሆኖ የሕግና የአሰራር ተጠያቂነቱ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።
የኤጀንሲውን አገልግሎት አሰጣጥ በሚመለከት ቅር የተሰኙ ነዋሪዎች በቀጥታ ቅሬታ ማቅረብ የሚችሉ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ማንኛውም ተገልጋይ በ7533 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ መስጠት የሚችል መሆኑንም ተናግረዋል።