የተፋሰስ ልማት ማህበራት ለዜጎች የስራ እድል ምንጭ መሆን ጀምረዋል -

ሀዋሳ (ኢዜአ) ጥር 15/2015 በለሙ ተፋሰሶች ላይ የተቋቋሙ የተፋሰስ ልማት ማህበራት ለዜጎች የስራ እድል መፍጠር መጀመራቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በደቡብ ክልል አቀፍ የተፋሰስ ልማት በሃላባ ዞን ዌራ ወረዳ ታችኛው በደኔ ዛሬ የተጀመረ ሲሆን በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን የተመለከተ ውይይት ተካሄዷል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ "ተጨባጭ ውጤት" ማምጣት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ የሚከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በተቀናጀ የሕብረተሰብ ተሳትፎ በመተግበር የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በተመረጡ ተፋሰሶች ላይ የአረንጓዴ አሻራ ስራውን በመተግበር ቀጣይነት ያለው ልማት ይከናወናል ብለዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤሊያስ በበኩላቸው ፤የተፈጥሮ ሃብት ስራው ግብርናው በዘላቂነት እንዲደግፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ስንዴን ጨምሮ ሌሎች ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ የተጀመረው ስራ እንዲሳካ የመሬትን ለምነት መጠበቅ እና በተቀናጀ ተፋሰስ ስራው ሕብረተሰቡን ባለቤት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም በለሙ ተፋሰሶች ላይ ከ1 ሺህ 500 በላይ የተፋሰስ ልማት ማህበራት መቋቋማቸውን ጠቅሰው፤ ማህበራቱን በማጠናከርና የገበያ ትስስር በመፍጠር ለዜጎች የስራ እድል ምንጭ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በለሙ ተፋሰሶች የፍራፍሬ ልማትን ጨምሮ፣ በእንስሳት እርባታና በሌሎች ዘርፎች በተለይ ወጣቶችን በማሰማራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ከዝናብ ጠባቂነት የተላቀቀ ዘመናዊ ግብርናን ለማጠናከር ያግዛል" ያሉት ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ናቸው፡፡

ባለፉት ዓመታት በክልሉ በተከናወነ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ስራ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም በ273 ሺህ 400 ሄክታር መሬት ላይ በሕብረተሰብ ተሳትፎ የተከናወነው የተፋሰስ ልማት ስራ ከ"4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ" እንደሚገመት ጠቅሰዋል፡፡

በዘንድሮ ዓመት በደቡብ ክልል 293 ሺህ 640 ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት መታቃዱን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም